ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 24:12-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ብዙ ጒልበት ቢፈስበትም፣የዝገቱ ክምር፣በእሳት እንኳ፣ ሊለቅ አልቻለም።

13. “ ‘የረከስሽው በብልግናሽ ነው፤ ቍጣዬ በአንቺ ላይ እስኪፈጸም ድረስ ከእንግዲህ ንጹሕ አትሆኚም፤ ከርኵሰትሽ ላነጻሽ ፈልጌ፣ መንጻት አልወደድሽምና።

14. “ ‘እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ የምሠራበትም ጊዜ ደርሶአል፤ ወደ ኋላ አልልም፤ አልራራም፤ አላመነታምም። እንደ መንገድሽና እንደ ተግባርሽ ይፈረድብሻል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

15. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

16. “የሰው ልጅ ሆይ፤ የዐይንህ ማረፊያ የሆነውን ነገር በመቅሠፍት እወስድብሃለሁ፤ አንተ ግን ዋይታ አታሰማ፤ አታልቅስ፤ እንባህንም አታፍስስ፤

17. ድምፅህን ዝቅ አድርገህ በሐዘን አንጐራጒር እንጂ ለሞተው አታልቅስ። ጥምጥምህን ከራስህ አታውርድ፤ ጫማህንም አታውልቅ፤ አፍህ ድረስ አትሸፋፈን፤ የዕዝን እንጀራም አትብላ።”

18. እኔም በማለዳ ለሕዝቡ ተናገርሁ፤ ሚስቴም ማታውኑ ሞተች፤ በማግሥቱም ጠዋት እንደ ታዘዝሁ አደረግሁ።

19. ሕዝቡም፣ “ይህን ስታደርግ ለእኛ የምታስተላልፈው መልእክት ምን እንደሆነ አትነግረንምን?” አሉኝ።

20. እኔም እንዲህ አልኋቸው፤ “የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

21. ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የኀይላችሁን ትምክሕት፣ የዐይናችሁ ማረፊያና የልባችሁ ደስታ የሆነውን መቅደሴን አረክሳለሁ። ትታችኋቸው የሄዳችሁ ወንድና ሴት ልጆቻችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።

22. እኔ እንዳደረግሁም ታደርጋላችሁ፤ አፋችሁ ድረስ አትሸፋፈኑም፤ የዕዝን እንጀራም አትበሉም፤

23. ጥምጥማችሁን ከራሳችሁ አታወርዱም፤ ጫማችሁንም አታወልቁም። በኀጢአታችሁ ትመነምናላችሁ፤ እርስ በርስ ታቃስታላችሁ እንጂ ሐዘን አትቀመጡም፤ አታለቅሱምም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 24