ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 23:32-49 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

32. “ጌታእግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ሰፊና ጥልቅ የሆነውን ጽዋ፣የእኅትሽን ጽዋ ትጠጪአለሽ፤ብዙም ስለሚይዝ ስድብና ነቀፌታትጠግቢአለሽ።

33. በእኅትሽ በሰማርያ ጽዋ፣በመፍረስና በጥፋት ጽዋ፣በስካርና በሐዘን ትሞዪአለሽ።

34. ትጠጪዋለሽ፤ ትጨልጪዋለሽም፤ከዚያም ጽዋውን ትሰባብሪዋለሽ፤ጡትሽንም ትቈራርጪአለሽ፤እኔ ተናግሬአለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

35. “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ረስተሽኛል፤ ወደ ኋላም ገሸሽ አድርገሽኛልና የብልግናሽንና የሴሰኝነትሽን ውጤት ትሸከሚአለሽ።’

36. እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በኦሖላና በኦሖሊባ ትፈርዳለህን? እንግዲያውስ ጸያፍ ተግባራቸውን ንገራቸው።

37. አመንዝረዋል እጃቸውም በደም ተበክሎአልና። ከጣዖቶቻቸው ጋር አመነዘሩ፤ የወለዱልኝን ልጆቻቸውን እንኳ ለእነርሱ መብል ይሆኑ ዘንድ በእሳት ሠውተውላቸዋል።

38. ደግሞም ይህን አደረጉብኝ፤ በዚያኑ ቀን ቤተ መቅደሴን አረከሱ፤ ሰንበታቴንም አቃለሉ።

39. ልጆቻቸውን ለጣዖቶቻቸው በሠዉባት ዕለት ወደ መቅደሴ ገብተው አረከሷት፤ እንግዲህ በቤቴ ውስጥ ያደረጉት እንዲህ ያለውን ነው።

40. “ከዚህም በላይ ወንዶች ከሩቅ እንዲመጡላቸው መልእክተኛ ላኩ፤ እነርሱም መጡ። አንቺም ገላሽን ታጥበሽ፣ ዐይንሽን ተኵለሽና በጌጣጌጥ ተውበሽ ጠበቅሻቸው።

41. በተዋበ ዐልጋ ላይ ተቀመጥሽ፤ ዕጣኔንና ዘይቴን ያኖርሽበትንም ጠረጴዛ ከዐልጋው ፊት ለፊት አደረግሽ።

42. “የሚፈነጥዙ ሰዎች ድምፅ በዙሪያዋ ነበር፤ ከሚያውኩ ሰዎች ጋር ከበረሓ የመጡ ሰካራሞች ነበሩ፤ በሴትየዋና በእኅትዋም ላይ አንባር፣ በራሳቸውም ላይ የተዋበ አክሊል አደረጉላቸው።

43. እኔም በአመንዝራነት ሰውነቷ ስላለቀው፣ ‘እርሷ ሕይወቷ ይኸው ስለ ሆነ እንደ ዝሙት ዐዳሪ ይጠቀሙባት’ አልሁ።

44. እነርሱም ከእርሷ ጋር ተኙ፤ ሰው ከአመንዝራ ሴት ጋር እንደሚተኛ ከእነዚያ ባለጌ ሴቶች፣ ከኦሖላና ከኦሖሊባ ጋር ተኙ።

45. ጻድቃን ግን ለአመንዝራና ለነፍሰ ገዳይ ሴቶች የሚገባቸውን ፍርድ ይፈርዱባቸዋል። አመንዝሮች ናቸውና፤ እጃቸውም በደም ተበክሎአል።

46. “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሕዝብን ቀስቅሰህ አምጣባቸው፤ ለሽብርና ለዝርፊያም አሳልፈህ ስጣቸው።

47. ሕዝቡ በድንጋይ ይወግራቸዋል፤ በገዛ ሰይፋቸው ይቈራ ርጣቸዋል፤ ወንድና ሴት ልጆቻቸውን ይገድላል፤ ቤቶቻቸውንም ያቃጥላል።

48. “ ‘ስለዚህ ሴቶች ሁሉ እንዲጠነቀቁና መጥፎ ፈለጋችሁን እንዳይከተሉ፣ ሴሰኝነትን ከምድሪቱ አጠፋለሁ።

49. የሴሰኝነታችሁን ዋጋ ታገኛላችሁ፤ ጣዖት በማምለክ ለፈጸማችሁት ኀጢአት ቅጣት ትሸከማላችሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።’ ”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 23