ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 23:18-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. ግልሙትናዋን በአደባባይ በፈጸመችና ዕርቃን በገለጠች ጊዜ ከእኅቷ ዘወር እንዳልሁ፣ ጠልቼአት ከእርሷም ዘወር አልሁ።

19. እርሷ ግን በግብፅ ያመነዘረችበት የወጣትነት ዘመኗ ትዝ እያላት የባሰ ዘማዊት ሆነች።

20. በዚያም አባለዘራቸው እንደ አህያ፣ የዘር ፍሰታቸውም እንደ ድንጒላ ፈረስ ዘር ፍሰት ከሆነ ውሽሞቿ ጋር አመነዘረች፤

21. በግብፅ ምድር ጒያሽን የታሸሽበትንና የወጣትነት ጡቶችሽን የተዳበስሽበትን የኰረዳነትሽን ብልግና ተመኘሽ።

22. “ስለዚህ፣ ኦሖሊባ ሆይ፤ ጌታእግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ጠልተሻቸው ከእነርሱ ዘወር ያልሽውን ውሽሞችሽን በአንቺ ላይ አስነሣለሁ፤ እነርሱንም ከየአቅጣጫው አመጣብሻለሁ፤

23. እነርሱም ባቢሎናውያንና ከለዳውያን ሁሉ፣ የፋቁድ፣ የሱሔና የቆዓ ሰዎች፣ ከእነርሱም ጋር አሦራውያን ሁሉ ናቸው። እነዚህም መልከ ቀና ጐበዛዝት ሲሆኑ፣ ሁላቸውም በፈረስ ላይ የተቀመጡ ገዦችና አዛዦች፣ የሠረገላ አዛዦችና ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖች ነበሩ።

24. እነርሱም የጦር መሣሪያ፣ ሠረገላና ጋሪ በመያዝ ብዙ ሕዝብ ሆነው ይመጡብሻል፤ ትላልቅና መለስተኛ ጋሻ በማንገብና የራስ ቍር በመድፋት በየአቅጣጫው ይሰለፉብሻል፤ እኔም ለፍርድ በእጃቸው አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ በሕጋቸውም መሠረት ይቀጡሻል።

25. የቅናት ቍጣዬን በአንቺ ላይ አመጣለሁ፤ እነርሱም በአንቺ ላይ በቍጣ ይወጣሉ፤ አፍንጫሽንና ጆሮሽን ይቈርጣሉ፤ ከአንቺ ወገን የተረፉትም በሰይፍ ይወድቃሉ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽን ይወስዱብሻል፤ የተረፉትንም እሳት ይበላቸዋል።

26. ልብስሽን ይገፉሻል፤ ምርጥ ጌጣጌጥሽንም ይወስዱብሻል።

27. በግብፅ የጀመርሽውን ብልግናና ሴሰኝነት ከአንቺ አስወግዳለሁ፤ አንቺም ዐይንሽን ወደ እነዚህ አታነሺም፤ ከእንግዲህ ግብፅን አታስቢም።

28. “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘እነሆ ተጸይፈሻቸው ከእነርሱ ዘወር ላልሽው ለጠላሻቸው አሳልፌ እሰጥሻለሁ።

29. እነርሱም በጥላቻ ይቀርቡሻል፤ የለፋሽበትንም ሁሉ ይቀሙሻል፤ ከማሕፀን እንደ ወጣሽ ዕርቃንሽን ያስቀሩሻል፤ የሴሰኝነትሽ ኀፍረት ይገለጣል። ብልግናሽና ገደብ የለሽ ርኵሰትሽ፣

30. ይህን አምጥተውብሻል፤ ከአሕዛብ ጋር በማመንዘር በጣዖቶቻቸው ረክሰሻልና።

31. በእኅትሽ መንገድ ስለ ሄድሽ የእርሷን ጽዋ በእጅሽ አስጨብጥሻለሁ።’

32. “ጌታእግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ሰፊና ጥልቅ የሆነውን ጽዋ፣የእኅትሽን ጽዋ ትጠጪአለሽ፤ብዙም ስለሚይዝ ስድብና ነቀፌታትጠግቢአለሽ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 23