ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 23:11-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. “እኅቷ ኦሖሊባ ይህን አይታ ነበር፤ ሆኖም በፍትወቷና በዘማዊነቷ ከእኅቷ የባሰች ብልሹ ሆነች።

12. ደግሞም ገዦችና አዛዦች፣ ጌጠኛ ልብስ የለበሱ ጦረኞች፣ ፈጣን ፈረሰኞችና፣ ሁሉም መልከ ቀና ከሆኑት አሦራውያን ጐበዛዝት ጋር አመነዘረች።

13. ይህችም እንደ ረከሰች አየሁ፤ ሁለቱም በአንድ መንገድ ሄዱ።

14. “በአመንዝራነቷ እየባሰች ሄደች፤ በደማቅ ቀይ ቀለም በግድግዳ ላይ የተቀረጹ የከለዳውያንን ወንዶች ምስል አየች፤

15. እነርሱም ወገባቸውን በቀበቶ የታጠቁና በራሳቸው ላይ ተንጠልጣይ ያለው ጥምጥም የጠመጠሙ ነበሩ፤ ሁሉም የከለዳውያን ተወላጆችና የባቢሎን ሠረገላ አዛዦች ይመስሉ ነበር።

16. ባየቻቸውም ጊዜ በፍትወት ተቃጠለች፤ ወደ ከላውዴዎን መልእክተኞች ላከችባቸው።

17. ባቢሎናውያንም መጥተው ወደ ፍቅር መኝታዋ ገቡ፤ በፍትወታቸውም አረከሷት፤ እርሷም በእነርሱ ከረከሰች በኋላ ጠልታቸው ከእነርሱ ዘወር አለች።

18. ግልሙትናዋን በአደባባይ በፈጸመችና ዕርቃን በገለጠች ጊዜ ከእኅቷ ዘወር እንዳልሁ፣ ጠልቼአት ከእርሷም ዘወር አልሁ።

19. እርሷ ግን በግብፅ ያመነዘረችበት የወጣትነት ዘመኗ ትዝ እያላት የባሰ ዘማዊት ሆነች።

20. በዚያም አባለዘራቸው እንደ አህያ፣ የዘር ፍሰታቸውም እንደ ድንጒላ ፈረስ ዘር ፍሰት ከሆነ ውሽሞቿ ጋር አመነዘረች፤

21. በግብፅ ምድር ጒያሽን የታሸሽበትንና የወጣትነት ጡቶችሽን የተዳበስሽበትን የኰረዳነትሽን ብልግና ተመኘሽ።

22. “ስለዚህ፣ ኦሖሊባ ሆይ፤ ጌታእግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ጠልተሻቸው ከእነርሱ ዘወር ያልሽውን ውሽሞችሽን በአንቺ ላይ አስነሣለሁ፤ እነርሱንም ከየአቅጣጫው አመጣብሻለሁ፤

23. እነርሱም ባቢሎናውያንና ከለዳውያን ሁሉ፣ የፋቁድ፣ የሱሔና የቆዓ ሰዎች፣ ከእነርሱም ጋር አሦራውያን ሁሉ ናቸው። እነዚህም መልከ ቀና ጐበዛዝት ሲሆኑ፣ ሁላቸውም በፈረስ ላይ የተቀመጡ ገዦችና አዛዦች፣ የሠረገላ አዛዦችና ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖች ነበሩ።

24. እነርሱም የጦር መሣሪያ፣ ሠረገላና ጋሪ በመያዝ ብዙ ሕዝብ ሆነው ይመጡብሻል፤ ትላልቅና መለስተኛ ጋሻ በማንገብና የራስ ቍር በመድፋት በየአቅጣጫው ይሰለፉብሻል፤ እኔም ለፍርድ በእጃቸው አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ በሕጋቸውም መሠረት ይቀጡሻል።

25. የቅናት ቍጣዬን በአንቺ ላይ አመጣለሁ፤ እነርሱም በአንቺ ላይ በቍጣ ይወጣሉ፤ አፍንጫሽንና ጆሮሽን ይቈርጣሉ፤ ከአንቺ ወገን የተረፉትም በሰይፍ ይወድቃሉ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽን ይወስዱብሻል፤ የተረፉትንም እሳት ይበላቸዋል።

26. ልብስሽን ይገፉሻል፤ ምርጥ ጌጣጌጥሽንም ይወስዱብሻል።

27. በግብፅ የጀመርሽውን ብልግናና ሴሰኝነት ከአንቺ አስወግዳለሁ፤ አንቺም ዐይንሽን ወደ እነዚህ አታነሺም፤ ከእንግዲህ ግብፅን አታስቢም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 23