ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 22:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2. “የሰው ልጅ ሆይ፤ አትፈርድባትምን? ደም በምታፈሰው በዚህች ከተማ ላይ አትፈርድባትምን? ጸያፍ ተግባሯን ፊት ለፊት ንገራት፤

3. እንዲህም በላት፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በመካከልሽ ደምን በማፍሰስና ጣዖታትን በመሥራት ራስሽን የምታረክሺ፣ ፍርድንም በራስሽ ላይ የምታፈጥኚ ከተማ ሆይ፤

4. ባፈሰስሽው ደም በድለሻል፤ በሠራሽውም ጣዖት ረክሰሻል፤ ከዚህም የተነሣ ቀንሽን አቅርበሻል፤ ዕድሜሽንም አሳጥረሻል። ስለዚህ ለአሕዛብ መዘባበቻ፣ ለአገሩም ሁሉ መሣለቂያ አደርግሻለሁ።

5. አንቺ የተዋረድሽና ሽብር የሞላብሽ ሆይ፤ በቅርብም በሩቅም ያሉ ይሣለቁብሻል።

6. “ ‘እነሆ በመካከልሽ ያለ እያንዳንዱ የእስራኤል መስፍን ደም ለማፍሰስ ሥልጣኑን ይጠቀማል።

7. አባቶችና እናቶች በውስጥሽ ተዋረዱ፤ መጻተኞች ተጨቈኑ፤ ድኻ አደጎችና መበለቶች ተንገላቱ።

8. ንዋያተ ቅድሳቴን አቃለልሽ፤ ሰንበታቴንም አረከስሽ።

9. ደምን ለማፍሰስ ወሬ የሚያቀብሉ በውስጥሽ አሉ፤ በኰረብታ ቤተ ጣዖት የተሠዋውን የሚበሉና ዝሙትን የሚፈጽሙ ሰዎች በመካከልሽ ይገኛሉ።

10. የአባታቸውን መኝታ የሚደፍሩ ሰዎች በውስጥሽ አሉ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ ባልሆኑበት በወር አበባቸው ጊዜ ሴቶችን በማስገደድ የሚደፍሩ በመካከልሽ ይገኛሉ።

11. በውስጥሽ አንዱ የባልንጀራውን ሚስት ያባልጋል፤ ሌላውም የልጁን ሚስት ያስነውራል፤ ሌላው ደግሞ የገዛ እኅቱ የሆነችውን የአባቱን ልጅ ይደፍራል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 22