ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 21:21-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. የባቢሎን ንጉሥ በጥንቈላ ምሪት ለማግኘት በመንታ መንገድ ላይ በሁለቱ ጐዳናዎች መጋጠሚያ ላይ ይቆማል፤ ቀስቶቹን በመወዝወዝ ዕጣ ይጥላል፤ አማልክቱን ያማክራል፤ ጒበትንም ይመረምራል።

22. የቅጥር መደርመሻ አምጥቶ እንዲያቆም፣ ለመግደል ትእዛዝ እንዲሰጥ፣ ፉከራ እንዲያሰማ፣ ቅጥር መደርመሻውን በከተሞች በር ላይ እንዲያደርግ፣ የዐፈር ድልድል እንዲያበጅና ምሽግ እንዲሠራ የኢየሩሳሌም ዕጣ በቀኝ እጁ ወጣ።

23. ይህም ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን ለገቡት የተሳሳተ ምሪት ይመስላል፤ እርሱ ግን በደላቸውን ያሳስባቸዋል፤ ማርኮም ይዞአቸው ይሄዳል።

24. “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እናንተ በምታደርጉት ሁሉ ኀጢአታችሁን በመግለጽ፣ በግልጽም በማመፅ በደላችሁን ስላሳሰባችሁ፣ እንዲህም ስላደረጋችሁ በምርኮ ትወሰዳላችሁ።

25. “ ‘አንተ የግፍ ጽዋህ የሞላ፣ የምትቀጣበት ቀን የደረሰ፣ ርኩስና ክፉ የእስራኤል መስፍን ሆይ፤

26. ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ጥምጥምህን አውልቅ፤ ዘውድህን ጣል፤ እንደ ከዚህ በፊቱ አይሆንም፤ ዝቅ ያለው ከፍ ይላል፤ ከፍ ያለውም ዝቅ ይላል።

27. ባድማ! ባድማ! ባድማ አደርጋታለሁ፤ የሚገባው ባለ መብት እስከሚመጣ ድረስ እንደ ቀድሞው አትሆንም፤ ለእርሱም ደግሞ እሰጣታለሁ።” ’

28. “አንተ የሰው ልጅ ሆይ! እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ስለ አሞናውያንና ስለ ስድባቸው ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘ሰይፍ! ሰይፍ!ሊገድል የተመዘዘ፣ሊያጠፋ የተጠረገ፣እንደ መብረቅ ሊያብረቀርቅ የተወለወለ፤

29. የታለመልህ የሐሰት ራእይ፣የተነገረልህ የውሸት ሟርት ቢኖርም፣የግፍ ጽዋቸው በሞላ፣ቀናቸው በደረሰ፣መታረድ በሚገባቸው ክፉዎች፣አንገት ላይ ይሆናል።

30. ሰይፉን ወደ ሰገባው መልሰው፤በተፈጠርህበት ምድር፣በተወለድህበትም አገር፣በዚያ እፈርድብሃለሁ።

31. መዓቴን በላይህ አፈሳለሁ፤የቍጣዬንም እሳት አነድብሃለሁ፣በጥፋት ለተካኑ፣ለጨካኞች ሰዎች አሳልፌ እሰጥሃለሁ።

32. ለእሳት ማገዶ ትሆናለህ፣ደምህ በምድርህ ይፈሳል፣ከእንግዲህ መታሰቢያ አይኖርህም፤እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና።’ ”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 21