ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 14:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከእስራኤል ሽማግሌዎች አንዳንዶቹ ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ።

2. የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

3. “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል፤ ክፋታቸውን እንደ ማሰናከያ ድንጋይ በፊታቸው አስቀምጠዋል፤ ታዲያ ከእኔ እንዳች ነገር እንዲጠይቁ ልፍቀድላቸውን?

4. ስለዚህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ማንኛውም እስራኤላዊ ጣዖትን በልቡ አኑሮ፣ ክፋቱንም የማሰናከያ ድንጋይ አድርጎ በፊቱ በማስቀመጥ ወደ ነቢይ ቢመጣ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖቱ ብዛት እመልስለታለሁ።

5. በጣዖቶቻቸው ምክንያት ከእኔ የተለዩትን የእስራኤልን ቤት ሁሉ ልብ ወደ ራሴ ለመመለስ ይህን አደርጋለሁ።’

6. “ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ንስሓ ግቡ ከጣዖቶቻችሁ ተመለሱ፤ ጸያፍ ተግባራችሁንም ሁሉ ተዉ።”

7. “ ‘ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ራሱን ከእኔ በመለየት ጣዖቶችን በልቡ አኑሮ፣ ክፋቱንም የማሰናከያ ድንጋይ በማድረግ በፊቱ አስቀምጦ ከእኔ ለመጠየቅ ወደ ነቢይ ቢመጣ፣ እኔ ራሴ እግዚአብሔር እመልስለታለሁ።

8. ፊቴን በክፋት ወደዚያ ሰው እመልሳለሁ፤ መቀጣጫና መተረቻ አደርገዋለሁ፤ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

9. “ ‘ነቢዩ ትንቢት ይናገር ዘንድ ቢታለል፣ ያንን ነቢይ ያታለልሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ክንዴን በእርሱ ላይ አነሣለሁ፤ ከሕዝቤ ከእስራኤል መካከልም አጠፋዋለሁ።

10. በደላቸው በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ነቢዩም እርሱን ሊጠይቀው ከመጣው ሰው ጋር እኩል በደለኛ ይሆናል።

11. ከእንግዲህ የእስራኤል ሕዝብ መንገድ ስቶ ከእኔ አይለይም፤ ተመልሶም በኀጢአቱ ሁሉ ራሱን አያረክስም። እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 14