ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 10:5-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ሁሉን የሚገዛ አምላክ ሲናገር እንደሚሰማው ድምፅ ዐይነት፣ የኪሩቤል ክንፎች ድምፅ እስከ ውጪው አደባባይ ድረስ ይሰማ ነበር።

6. እግዚአብሔር በፍታ የለበሰውን ሰው፣ “ከኪሩቤል ዘንድ ከመንኰራኵሮቹ መካከል እሳት ውሰድ” ብሎ ባዘዘው ጊዜ፣ ሰውዬው ወደ ውስጥ ገብቶ በአንዱ መንኰራኵር አጠገብ ቆመ።

7. ከኪሩቤልም አንዱ በመካከላቸው ወዳለው እሳት እጁን ዘርግቶ ጥቂት ወሰደ፤ በፍታ በለበ ሰው ሰው እጅ ላይ አኖረው፤ እርሱም ይዞ ወጣ።

8. ከኪሩቤል ክንፎች ሥር የሰው እጅ የሚመስል ይታይ ነበር።

9. እኔም አየሁ፤ እነሆ፤ በኪሩቤል አጠገብ አራት መንኰራኵሮች ነበሩ፤ በእያንዳንዱ ኪሩብ አጠገብ አንድ መንኰራኵር ነበር፤ የመንኰራኵሮቹም መልክ እንደ ቢረሌያን ጸባርቅ ነበር።

10. የአራቱም መልክ ይመሳሰል ነበር፤ እያንዳንዱም መንኰራኵር በመንኰራኵር ውስጥ ተሰክቶ የተሠራ ይመስል ነበር።

11. መንኰራኵሮቹ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜም ኪሩቤል ወደ ዞሩበት ወደ አራቱ አቅጣጫ ሁሉ መሄድ ይችሉ ነበር፤ ኪሩቤል በሚሄዱበት ጊዜ መንኰራኵሮቹ ወዲያ ወዲህ አይሉም ነበር፤ ኪሩቤል በሚሄዱበት ጊዜ ወዲያ ወዲህ ሳይሉ፣ ራስ ወደ ዞረበት ወደ ማንኛውም አቅጣጫ ይጓዙ ነበር።

12. ጀርባቸውን፣ እጃቸውን፣ ክንፋቸውን ጨምሮ መላ ሰውነታቸው እንዲሁም አራቱ መንኰራኵሮቻቸው በጠቅላላ በዐይን የተሞሉ ነበሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 10