ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 10:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እኔም አየሁ፤ እነሆ ከኪሩቤል ራስ በላይ ካለው ጠፈር ከፍ ብሎ፣ የሰንፔር ዙፋን የሚመስል ነገር ነበረ።

2. እግዚአብሔርም በፍታ የለበሰውን ሰው፣ “በኪሩቤል ሥር ወዳሉት መንኰራኵሮች መካከል ግባ፤ በኪሩቤል መካከል ካለውም የእሳት ፍም እጅህን ሞልተህ ዝገን፤ በከተማዪቱም ላይ በትነው” አለው። ሰውዬውም እያየሁት ገባ።

3. ሰውዬው ወደ ውስጥ በገባ ጊዜ፣ ኪሩቤል በቤተ መቅደሱ ውስጥ በደቡብ በኩል ቆመው ነበር፤ ደመናም ውስጠኛውን አደባባይ ሞላ።

4. የእግዚአብሔርም ክብር ከነበረበት ከኪሩቤል በላይ ተነሥቶ ወደ ቤተ መቅደሱ መድረክ ሄደ፤ ደመናው ቤተ መቅደሱን ሞላ፤ አደባባዩም በእግዚአብሔር ክብር ብርሃን ተሞላ።

5. ሁሉን የሚገዛ አምላክ ሲናገር እንደሚሰማው ድምፅ ዐይነት፣ የኪሩቤል ክንፎች ድምፅ እስከ ውጪው አደባባይ ድረስ ይሰማ ነበር።

6. እግዚአብሔር በፍታ የለበሰውን ሰው፣ “ከኪሩቤል ዘንድ ከመንኰራኵሮቹ መካከል እሳት ውሰድ” ብሎ ባዘዘው ጊዜ፣ ሰውዬው ወደ ውስጥ ገብቶ በአንዱ መንኰራኵር አጠገብ ቆመ።

7. ከኪሩቤልም አንዱ በመካከላቸው ወዳለው እሳት እጁን ዘርግቶ ጥቂት ወሰደ፤ በፍታ በለበ ሰው ሰው እጅ ላይ አኖረው፤ እርሱም ይዞ ወጣ።

8. ከኪሩቤል ክንፎች ሥር የሰው እጅ የሚመስል ይታይ ነበር።

9. እኔም አየሁ፤ እነሆ፤ በኪሩቤል አጠገብ አራት መንኰራኵሮች ነበሩ፤ በእያንዳንዱ ኪሩብ አጠገብ አንድ መንኰራኵር ነበር፤ የመንኰራኵሮቹም መልክ እንደ ቢረሌያን ጸባርቅ ነበር።

10. የአራቱም መልክ ይመሳሰል ነበር፤ እያንዳንዱም መንኰራኵር በመንኰራኵር ውስጥ ተሰክቶ የተሠራ ይመስል ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 10