ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 9:8-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ንጉሥ ሆነህ እንድትገዛ፣ በአንተ ደስ የተሰኘውና በዙፋኑ ላይ ያስቀመጠህ አምላክህ እግዚአብሔር ቡሩክ ይሁን፤ አምላክህ ለእስራኤል ካለው ፍቅርና ለዘላለም ሊያጸናቸው ካለው ፍላጎት የተነሣ፣ ፍትሕና ጽድቅ እንዲሰፍን ታደርግ ዘንድ አንተን በላያቸው ላይ አንግሦሃልና።”

9. ከዚያም ለንጉሡ አንድ መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ፣ እጅግ ብዙ ቅመማ ቅመምና የከበሩ ድንጋዮች ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሥ ሰሎሞን እንደሰጠችው ዐይነት ቅመማ ቅመም ያለ ከቶ አልነበረም።

10. የኪራም ሰዎችና የሰሎሞን ሰዎች ወርቅ ከኦፊር እንደዚሁም ሰንደልና የከበሩ ድንጋዮች አመጡ።

11. ንጉሡም የሰንደሉን እንጨት ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ለቤተ መንግሥቱ ደረጃ መሥሪያ እንደዚሁም ለመዘምራኑ የመሰንቆና የበገና መሥሪያ አደረገው፤ ይህን የመሰለ ነገር በይሁዳ ምድር ከቶ አልታየም።

12. ንጉሥ ሰሎሞን ለሳባ ንግሥት የፈለገችውንና የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣት፤ ስጦታውም እርስዋ ካመጣችለት በላይ ነበር። ከዚያም ከአጃቢዎቿ ጋር ወደ አገሯ ተመለሰች።

13. ሰሎሞን በየዓመቱ የሚቀበለው ወርቅ ክብደቱ ስድስት መቶ ሥልሳ ስድስት መክሊት ነበር።

14. ይህም ከታላላቅና ከተራ ነጋዴዎች ከሚገባው ቀረጥ ሌላ ነበር፤ እንዲሁም መላው የዐረብ ነገሥታትና የገዛ ምድሩ አገረ ገዦች ለሰሎሞን ወርቅና ብር ያመጡለት ነበር።

15. ንጉሥ ሰሎሞን ሁለት መቶ ከጥፍጥፍ ወርቅ የተሠራ ታላላቅ ጋሻዎች አበጀ፤ በእያንዳንዱም ጋሻ የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ስድስት መቶ ሰቅል ነበር።

16. እንዲሁም ሦስት መቶ ትንንሽ ጋሻዎች በጥፍጥፍ ወርቅ ሠራ፤ በእነዚህም በእያንዳንዳቸው የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ሦስት መቶ ሰቅል ነበር። ንጉሡም ጋሻዎቹን “የሊባኖስ ደን” በተባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ አኖራቸው።

17. ከዚያም ንጉሡ በዝሆን ጥርስ ያጌጠና በንጹሕ ወርቅ የተለበጠ ትልቅ ዙፋን ሠራ።

18. ዙፋኑ ስድስት መውጫ መውረጃ ደረጃዎች ሲኖሩት፣ ከዙፋኑ ጋር የተያያዘ ከወርቅ የተሠራ የእግር መርገጫ ነበረው። መቀመጫውም ግራና ቀኙ መደገፊያ ያለው ሆኖም ከመደገፊያዎቹም አጠገብ አንዳንድ አንበሳ ቆሞ ነበር።

19. እንዲሁም በስድስቱ ደረጃዎች ዳርና ዳር ላይ አንዳንድ አንበሳ፣ ባጠቃላይ አሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ ይህን የመሰለ ዙፋን በየትኛውም አገር ተሠርቶ አያውቅም።

20. ንጉሥ ሰሎሞን የሚጠጣባቸው ዕቃዎች በሙሉ ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ “የሊባኖስ ደንቃ ተብሎ በሚጠራው ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበሩትም ዕቃዎች ሁሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ በሰሎሞን ዘመን ብር ዋጋ እንደሌለው ስለሚቈጠር ከብር የተሠራ አንድም ነገር አልነበረም።

21. ንጉሡ በኪራም ሰዎች የሚነዱ የንግድ መርከቦች ነበሩት፤ እነዚህም በየሦስት ዓመቱ አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብር፣ የዝሆን ጥርስ፣ ጦጣዎችና ዝንጀሮዎች እየያዙ ይመለሱ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 9