ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 9:15-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ንጉሥ ሰሎሞን ሁለት መቶ ከጥፍጥፍ ወርቅ የተሠራ ታላላቅ ጋሻዎች አበጀ፤ በእያንዳንዱም ጋሻ የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ስድስት መቶ ሰቅል ነበር።

16. እንዲሁም ሦስት መቶ ትንንሽ ጋሻዎች በጥፍጥፍ ወርቅ ሠራ፤ በእነዚህም በእያንዳንዳቸው የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ሦስት መቶ ሰቅል ነበር። ንጉሡም ጋሻዎቹን “የሊባኖስ ደን” በተባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ አኖራቸው።

17. ከዚያም ንጉሡ በዝሆን ጥርስ ያጌጠና በንጹሕ ወርቅ የተለበጠ ትልቅ ዙፋን ሠራ።

18. ዙፋኑ ስድስት መውጫ መውረጃ ደረጃዎች ሲኖሩት፣ ከዙፋኑ ጋር የተያያዘ ከወርቅ የተሠራ የእግር መርገጫ ነበረው። መቀመጫውም ግራና ቀኙ መደገፊያ ያለው ሆኖም ከመደገፊያዎቹም አጠገብ አንዳንድ አንበሳ ቆሞ ነበር።

19. እንዲሁም በስድስቱ ደረጃዎች ዳርና ዳር ላይ አንዳንድ አንበሳ፣ ባጠቃላይ አሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ ይህን የመሰለ ዙፋን በየትኛውም አገር ተሠርቶ አያውቅም።

20. ንጉሥ ሰሎሞን የሚጠጣባቸው ዕቃዎች በሙሉ ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ “የሊባኖስ ደንቃ ተብሎ በሚጠራው ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበሩትም ዕቃዎች ሁሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ በሰሎሞን ዘመን ብር ዋጋ እንደሌለው ስለሚቈጠር ከብር የተሠራ አንድም ነገር አልነበረም።

21. ንጉሡ በኪራም ሰዎች የሚነዱ የንግድ መርከቦች ነበሩት፤ እነዚህም በየሦስት ዓመቱ አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብር፣ የዝሆን ጥርስ፣ ጦጣዎችና ዝንጀሮዎች እየያዙ ይመለሱ ነበር።

22. ንጉሥ ሰሎሞን በሀብትም ሆነ በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ የበለጠ ነበር።

23. የምድር ነገሥታት ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረውን ጥበብ ለመስማት ከሰሎሞን ጋር መገናኘት ይፈልጉ ነበር።

24. በየዓመቱ ወደ እርሱ የሚመጡትም ሁሉ የብርና የወርቅ ዕቃ፣ የልብስ፣ የጦር መሣሪያና የቅመማ ቅመም እንደዚሁም የፈረስና የበቅሎ ገጸ በረከት ያመጡለት ነበር።

25. ሰሎሞን አራት ሺ የፈረሶችና የሠረገሎች ጋጥ ነበረው፤ እንዲሁም በሚኖርበት በኢየሩሳሌምና በሰረገላ ከተሞች አሥራ ሁለት ሺህ ፈረሶች ነበሩት።

26. እርሱም ከኤፍራጥስ ወንዝ እስከ ፍልስጥኤም ምድርና እስከ ግብፅ ዳርቻ ድረስ ባሉት ነገሥታት ሁሉ ላይ ገዛ።

27. ንጉሡ በኢየሩሳሌም ብሩን እንደ ማንኛውም ድንጋይ፣ የዝግባውንም ዕንጨት ብዛት በየኰረብታው ግርጌ እንደሚበቅል ሾላ አደረገው።

28. ለሰሎሞን ከግብፅና ከሌሎች አገሮች ሁሉ ፈረሶች ያመጡለት ነበር።

29. ሰሎሞን በዘመነ መንግሥቱ የሠራው ሌላው ነገር በነቢዩ በናታን ታሪክና በሴሎናዊው በአሒያ ትንቢት እንዲሁም ባለ ራእዩ አዶ ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓም ባየው ራእይ ውስጥ የተጻፈ አይደለምን?

30. ሰሎሞን በኢየሩሳሌም ተቀምጦ በእስራኤል ሁሉ ላይ አርባ ዓመት ነገሠ።

31. ከዚያም እንደ አባቶቹ አንቀላፋ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁም ሮብዓም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 9