ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 6:4-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. እንዲህም አለ፤“ለአባቴ ለዳዊት በቃሉ የሰጠውን ተስፋ በእጁ የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እንዲህ ብሏልና፤

5. ‘ሕዝቤን ከግብፅ ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ፣ ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ ይሠራበት ዘንድ ከማናቸውም የእስራኤል ነገድ ከተሞች አንድም አልመረጥሁም፤ ወይም የሕዝቤ የእስራኤል መሪ ይሆን ዘንድ ማንንም አልመረጥሁም።

6. አሁን ግን ስሜ በዚያ እንዲሆን ኢየሩሳሌምን፣ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲገዛም ዳዊትን መርጫለሁ።”

7. “አባቴ ዳዊት፣ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልቡ አስቦ ነበር፤

8. እግዚአብሔር ግን፣ ለአባቴ ለዳዊት እንዲህ አለው፤ ለስሜ ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልብህ አስበህ ነበር፤ ይህን በልብህ በማሰብህ መልካም አድርገሃል፤

9. ይሁን እንጂ ቤተ መቅደሱን የምትሠራው አንተ አይደለህም፤ ለስሜ ቤተ መቅደስ የሚሠራልኝ ከአብራክህ የሚከፈለው፣ የገዛ ልጅህ ነው።’

10. “እግዚአብሔርም የተናገረውን ቃል ፈጽሞአል፤ እኔም እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቼ፣ በእስራኤል ዙፋን ላይ ተቀምጫለሁ፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔርም ስም ቤተ መቅደስ ሠርቻለሁ።

11. በዚያም እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያደረገው ኪዳን ያለበትን ታቦት አኑሬአለሁ።”

12. ከዚህ በኋላ ሰሎሞን መላው የእስራኤል ጉባኤ ባሉበት በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት እጆቹን ዘርግቶ ቆመ።

13. ሰሎሞንም ርዝመቱ አምስት ክንድ፣ ወርዱ አምስት ክንድ፣ ከፍታውም ሦስት ክንድ የሆነ የናስ መድረክ በውጭው አደባባይ መካከል አሠርቶ ነበር፤ በመድረኩም ላይ ወጥቶ በመቆም በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ተንበርክኮ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘረጋ፣

14. እንዲህም አለ፤“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልባቸው በመንገድህ ከሚሄዱት ባሪያዎችህ ጋር የፍቅር ኪዳንህን የምትጠብቅ በሰማይም ሆነ በምድር እንደ አንተ ያለ አምላክ የለም፤

15. ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ አጽንተሃል፤ በአፍህ የተናገርኸውን ዛሬም እንደሆነው በእጅህ ፈጸምኸው።

16. “አሁንም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት፣ ‘ልጆችህ አንተ እንደ አደረግኸው ሁሉ በሚያደርጉት ሁሉ ሕጌን በመጠበቅ በፊቴ ቢመላለሱ፣ በእራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚቀመጥ ሰው ከቶ አታጣም’ ብለህ የሰጠኸውን ተስፋ አጽናለት።

17. እንግዲህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፣ ለባሪያህ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ይፈጸም።

18. “በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፤ ሰማያትና ሰማየ ሰማያት እንኳ አንተን ሊይዙህ አይችሉም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምንኛ ያንስ!

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 6