ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 6:18-38 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. “በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፤ ሰማያትና ሰማየ ሰማያት እንኳ አንተን ሊይዙህ አይችሉም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምንኛ ያንስ!

19. ይሁን እንጂ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ የባሪያህን ጸሎትና ስለ ምሕረት ያቀረበውን ልመና አድምጥ፤ ባሪያህ በፊትህ የሚያቀርበውን ጩኸትና ጸሎት ስማ።

20. ስምህ እንደሚጠራበት ወደ ተናገርኸው ወደዚህ ቤተ መቅደስ ዓይኖችህ በቀንም በሌሊትም የተገለጡ ይሁኑ፤ ባሪያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውንም ጸሎት ስማ።

21. ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ በሚጸል ዩበትም ጊዜ ልመናቸውን ስማ፤ ከማደሪያህ ከሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል።

22. አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢበድልና እንዲምል ቢጠየቅ፣ እርሱም መጥቶ በቤተ መቅደሱ በመሠዊያህ ፊት ቢምል፣

23. ከሰማይ ሆነህ ስማ፤ አድርግም። በደለኛውን፣ በደሉን በራሱ ላይ አድርገህ እንደ ሥራው በመክፈል በባሪያዎችህ መካከል ፍረድ። ንጹሑም በደለኛ አለመሆኑን አስታውቅ፤ እንደ ንጽሕናውም ክፈለው።

24. “ሕዝብህ እስራኤል አንተን ከመበደላቸው የተነሣ በጠላቶቻቸው ፊት ድል ቢሆኑ፣ ወደ አንተ ተመልሰውም በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ በፊትህ በመጸለይና ልመናቸውን በማቅረብ ስምህን ቢጠሩ፣

25. በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለእነርሱና ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸውም ምድር መልሳቸው።

26. “ሕዝብህ አንተን ከመበደላቸው የተነሣ፣ ሰማያት ተዘግተው ዝናብ ባይዘንብ፣ አንተ ስለአስጨነቅሃቸው ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩ፣ ስምህን ቢጠሩና ከኀጢአታቸው ቢመለሱ፣

27. በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የባሪያዎችህን የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ የሚኖሩበትን ቀናውን መንገድ አስተምራቸው፤ ለሕዝብህ ርስት አድርገህ በሰጠኸውም ምድር ላይ ዝናብን ላክ።

28. “በምድሪቱ ላይ ራብ ወይም ቸነፈር ወይም ዋግ ወይም አረማሞ ወይም አንበጣ ወይም ኩብኩባ በሚወርድባት ጊዜ፣ ወይም ደግሞ በየትኛውም ከተማቸው ሳሉ ጠላት በሚከባቸው ጊዜ፣ ወይም ማናቸውም አደጋ ወይም ደዌ በሚደርስባቸው ጊዜ፣

29. ከሕዝብህ ከእስራኤል ማንም ሰው ጭንቀቱና ሕመሙ ተሰምቶት፣ እጁን ወደዚህ ቤተ መቅደስ በመዘርጋት ጸሎትና ልመና ቢያቀርብ፣

30. በሰማይ በማደሪያህ ሆነህ ስማ፤ ይቅርም በል፤ የሰውን ልብ የምታውቅ አንተ ብቻ ስለ ሆንህ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን ክፈለው፤

31. ይህም ለአባቶቻችን በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ አንተን እንዲፈሩህና በመንገዶችህ እንዲሄዱ ነው።

32. “ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ ባዕድ ሰው ስለ ታላቁ ስምህ፣ ስለ ኀያሉ እጅህና ስለ ተዘረጋው ክንድህ ሰምቶ ከሩቅ አገር በመምጣት ወደዚህ ቤተ መቅደስ በሚጸልይበት ጊዜ፣

33. በሰማይ በማደሪያህ ሆነህ ስማ፤ የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንደገዛ ሕዝብህ እንደ እስራኤል፣ ስምህን በማወቅ እንዲፈሩህ፣ የሠራሁትም ይህ ቤት ስምህ የሚጠራበት ቤት መሆኑን እንዲያውቁ ባዕዱ ሰው የሚጠይቅህን ሁሉ አድርግ።

34. “ሕዝብህ አንተ በምትልካቸው ቦታ ሁሉ ጠላቶቻቸውን ለመውጋት በሚወጡበት ጊዜ፣ አንተ ወደ መረጥኻት ወደዚህች ከተማ፣ እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ወደ አንተ ቢጸልዩ፣

35. ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ ስማ፤ የጠየቁህንም አድርግላቸው።

36. “መቼም የማይበድል ሰው የለምና፣ አንተን በበደሉህ ጊዜ፣ ተቈጥተሃቸው ሩቅ ወይም ቅርብ ወደ ሆነ አገር በምርኮ ለሚወስዳቸው ጠላት አሳልፈህ ብትሰጣቸው፣

37. በተማረኩበት አገር ሆነው የልብ ጸጸት ተሰምቶአቸው ንስሐ ቢገቡና በምርኮ ሳሉ፣ ‘ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል’ ቢሉ፣

38. ተማርከው በሚኖሩበትም ምድር ሆነው በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹምም ነፍሳቸው ቢመለሱና ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸው ምድር፣ አንተም ወደ መረጥኻት ከተማና እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ቢጸልዩ፣

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 6