ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 6:11-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. በዚያም እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያደረገው ኪዳን ያለበትን ታቦት አኑሬአለሁ።”

12. ከዚህ በኋላ ሰሎሞን መላው የእስራኤል ጉባኤ ባሉበት በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት እጆቹን ዘርግቶ ቆመ።

13. ሰሎሞንም ርዝመቱ አምስት ክንድ፣ ወርዱ አምስት ክንድ፣ ከፍታውም ሦስት ክንድ የሆነ የናስ መድረክ በውጭው አደባባይ መካከል አሠርቶ ነበር፤ በመድረኩም ላይ ወጥቶ በመቆም በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ተንበርክኮ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘረጋ፣

14. እንዲህም አለ፤“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልባቸው በመንገድህ ከሚሄዱት ባሪያዎችህ ጋር የፍቅር ኪዳንህን የምትጠብቅ በሰማይም ሆነ በምድር እንደ አንተ ያለ አምላክ የለም፤

15. ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ አጽንተሃል፤ በአፍህ የተናገርኸውን ዛሬም እንደሆነው በእጅህ ፈጸምኸው።

16. “አሁንም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት፣ ‘ልጆችህ አንተ እንደ አደረግኸው ሁሉ በሚያደርጉት ሁሉ ሕጌን በመጠበቅ በፊቴ ቢመላለሱ፣ በእራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚቀመጥ ሰው ከቶ አታጣም’ ብለህ የሰጠኸውን ተስፋ አጽናለት።

17. እንግዲህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፣ ለባሪያህ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ይፈጸም።

18. “በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፤ ሰማያትና ሰማየ ሰማያት እንኳ አንተን ሊይዙህ አይችሉም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምንኛ ያንስ!

19. ይሁን እንጂ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ የባሪያህን ጸሎትና ስለ ምሕረት ያቀረበውን ልመና አድምጥ፤ ባሪያህ በፊትህ የሚያቀርበውን ጩኸትና ጸሎት ስማ።

20. ስምህ እንደሚጠራበት ወደ ተናገርኸው ወደዚህ ቤተ መቅደስ ዓይኖችህ በቀንም በሌሊትም የተገለጡ ይሁኑ፤ ባሪያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውንም ጸሎት ስማ።

21. ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ በሚጸል ዩበትም ጊዜ ልመናቸውን ስማ፤ ከማደሪያህ ከሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል።

22. አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢበድልና እንዲምል ቢጠየቅ፣ እርሱም መጥቶ በቤተ መቅደሱ በመሠዊያህ ፊት ቢምል፣

23. ከሰማይ ሆነህ ስማ፤ አድርግም። በደለኛውን፣ በደሉን በራሱ ላይ አድርገህ እንደ ሥራው በመክፈል በባሪያዎችህ መካከል ፍረድ። ንጹሑም በደለኛ አለመሆኑን አስታውቅ፤ እንደ ንጽሕናውም ክፈለው።

24. “ሕዝብህ እስራኤል አንተን ከመበደላቸው የተነሣ በጠላቶቻቸው ፊት ድል ቢሆኑ፣ ወደ አንተ ተመልሰውም በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ በፊትህ በመጸለይና ልመናቸውን በማቅረብ ስምህን ቢጠሩ፣

25. በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለእነርሱና ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸውም ምድር መልሳቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 6