ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 36:12-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. እርሱም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ የእግዚአብሔርን ቃል በተናገረው በነቢዩ በኤርምያስ ፊትም ራሱን ዝቅ አላደረገም።

13. እንደዚሁም በእግዚአብሔር ስም አምሎት በነበረው በንጉሥ ናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ፤ አንገቱን አደነደነ፤ ልቡንም አጠነከረ እንጂ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አልተመለሰም።

14. ከዚህም ላይ የካህናቱና የሕዝቡ መሪዎች ሁሉ፣ አስጸያፊ የሆኑትን የአሕዛብን ልማዶች በመከተልና በኢየሩሳሌም የተቀደሰውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በማርከስ፣ ባለ መታመናቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሱ ሄዱ።

15. የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ፣ መልእክተኞቹን ይልክ ነበር፤

16. እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቊጣ በሕዝቡ ላይ እስኪነሣሣና ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ላይ ተሳለቁ፤ ቃሉን ናቁ፤ ነቢያቱንም አቃለሉ።

17. ስለዚህ የባቢሎናውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ወጣቶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ፈጀ፤ ወጣቱንም ሆነ ወጣቲቱን፣ ሽማግሌውንም ሆነ በዕድሜ የገፋውን አላስቀረም፤ እግዚአብሔር ሁሉንም ለናቡከደናፆር አሳልፎ ሰጠው።

18. እርሱም ትልልቁንም ሆነ ትንንሹን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃ በሙሉ፣ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሀብት፣ የንጉሡንና የሹማምቱን ሀብት ሁሉ ወደ ባቢሎን አጋዘ።

19. የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በእሳት አቃጠሉ፤ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች አፈረሱ፤ ቤተ መንግሥቶቹን በሙሉ አቃጠሉ፤ በዚያ የነበረውንም የከበረ ዕቃ በሙሉ አጠፉ።

20. ከሰይፍ የተረፉትን ቅሬታዎች በምርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፤ እስከ ፋርስ መንግሥት መነሣትም ድረስ የእርሱና የልጆቹ አገልጋዮች ሆኑ።

21. ምድሪቱም የሰንበት ዕረፍት አገኘች፤ በኤርምያስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ ሰባው ዓመት እስኪያበቃ ድረስ፣ ባድማ በነበረችበት ዘመን ሁሉ ዐረፈች።

22. በኤርምያስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ዓመት፣ በግዛቱ ሁሉ ዐዋጅ እንዲያስነግርና ይህም እንዲጻፍ እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አነሣሣ፤ እርሱም እንዲህ አለ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 36