ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 27:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኢዮአታም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ሲሆን፣ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ። እናቱም ኢየሩሳ የተባለች የሳዶቅ ልጅ ነበረች።

2. አባቱ ዖዝያን እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ይሁን እንጂ እንደ አባቱ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አልገባም። ሕዝቡም በበደሉ እንደ ገፋበት ነበር።

3. ኢዮአታም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የላይኛውን በር እንደ ገና ሠራው፤ በዖፌልም በኩል ባለው ቅጥር ላይ፣ አያሌ የማሻሻል ተግባር አከናወነ።

4. በይሁዳ ኰረብታዎች ላይ ከተሞችን፣ ደን በለበሱ ስፍራዎችም ምሽጎችንና ማማዎችን ሠራ።

5. ኢዮአታም የአሞናውያንን ንጉሥ ወግቶ ድል አደረጋቸው። በዚያ ዓመትም አሞናውያን አንድ መቶ መክሊት ጥሬ ብር፣ ዐሥር ሺህ ቆሮስ ስንዴና ዐሥር ሺህ ቆሮስ ገብስ ገበሩለት። አሞናውያን በሁለተኛውና በሦስተኛው ዓመት ይህንኑ ግብር አመጡለት።

6. ኢዮአታም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት በታማኝነት ስለተመላለሰ፣ እየበረታ ሄደ።

7. በኢዮአታም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባር፣ ያደረጋቸው ጦርነቶችና የሠራቸው ነገሮች በሙሉ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።

8. እርሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 27