ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 2:5-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. “አምላካችን ከሌሎች አማልክት ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ስለ ሆነ፣ የምሠራውም ቤተ መቅደስ ታላቅ ይሆናል።

6. ነገር ግን ሰማይና ከሰማያት በላይ ያለው ሰማይ እንኳን እርሱን ይይዘው ዘንድ አይችልምና፣ ቤተ መቅደስ ሊሠራለት የሚችል ማነው? በፊቱ ዕጣን የሚታጠንበትን እንጂ ቤተ መቅደስ እሠራለት ዘንድ እኔ ማን ነኝ?

7. “ስለዚህ አንተ በወርቅና በብር፣ በናስና በብረት፣ በሐምራዊና በደማቅ ቀይ፣ በሰማያዊም ግምጃ ሥራ ዕውቀት ያለውን እንዲሁም አባቴ ዳዊት ካዘጋጃቸው ከእኔ የእጅ ባለ ሙያዎች ጋር በይሁዳና በኢየሩሳሌም የቅርጻ ቅርጽ ጥበብ ሥራ የሚሠራ ሰው ላክልኝ።

8. ሰዎችህ ከሊባኖስ እንጨት በመቍረጥ ሥራ ዐዋቂዎች መሆናቸውን ስለማውቅ፣ ከሊባኖስ የዝግባ፣ የጥድና የሰንደል ዕንጨትም ላክልኝ፤ ሰዎቼም ከሰዎችህ ጋር አብረው ይሠራሉ።

9. የምሠራው ቤተ መቅደስ ትልቅና እጅግ ውብ መሆን ስላለበት፣ ብዙ ጠርብ ያዘጋጁልኛልና።

10. ዕንጨቱን ለሚቈርጡ አገልጋዮችህ ሃያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ ዱቄት፣ ሃያ ሺህ የባዶስ መስፈሪያ ወይን ጠጅና ሃያ ሺህ የባዶስ መስፈሪያ ዘይት እሰጣለሁ።”

11. የጢሮስ ንጉሥ ኪራምም ለሰሎሞን እንዲህ ሲል በደብዳቤ መለሰለት፤“እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለሚወድድ አንተን በእነርሱ ላይ አነገሠህ፤”

12. ኪራምም በመቀጠል እንዲህ አለ፤“ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ! ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስን፣ ለራሱም ቤተ መንግሥትን የሚሠራ፣ ብልኅነትንና ማስተዋልን የተሞላ ጥበበኛ ልጅ ለንጉሥ ዳዊት ሰጥቶአልና።

13. “እጅግ ብልሃተኛ የሆነውን ኪራም አቢን ልኬልሃለሁ፤

14. እርሱም እናቱ ከዳን ወገን፣ አባቱም የጢሮስ አገር ሰው ነው፤ በወርቅና በብር፣ በናስና በብረት፣ በድንጋይና በዕንጨት፤ እንዲሁም በሐምራዊና በሰማያዊ፣ በቀይ ግምጃና በቀጭን በፍታ ሥራ የሠለጠነ ሲሆን፣ በልዩ ልዩ ቅርጻ ቅርጽ ሥራ ልምድ ያካበተና የተሰጠውን ማናቸውንም ንድፍ በሥራ መተርጐም የሚችል ባለ ሙያ ነው። እርሱም ከአንተ የእጅ ሥራ ባለሙያዎችና ከጌታዬ ከአባትህ የእጅ ሥራ ባለ ሙያዎች ጋር አብሮ ይሠራል።

15. “አሁንም ጌታዬ በሰጠው ተስፋ መሠረት ስንዴውንና ገብሱን፣ የወይራ ዘይቱንና የወይን ጠጁን ለአገልጋዮቹ ይላክ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 2