ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 2:4-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ሽታው ደስ የሚያሰኝ ዕጣን በፊቱ የሚታጠንበትን፣ የተቀደሰ እንጀራ በየጊዜው የሚቀርብበትን፣ በየጧቱና በየማታው፣ በየሰንበቱና በየመባቻው እንዲሁም በተወሰኑት በአምላካችን በእግዚአብሔር በዓላት የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን ቤተ መቅደስ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ሠርቼ እቀድስ ዘንድ አስቤአለሁ። ይህም ለእስራኤል የዘላለም ሥርዐት ነው።

5. “አምላካችን ከሌሎች አማልክት ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ስለ ሆነ፣ የምሠራውም ቤተ መቅደስ ታላቅ ይሆናል።

6. ነገር ግን ሰማይና ከሰማያት በላይ ያለው ሰማይ እንኳን እርሱን ይይዘው ዘንድ አይችልምና፣ ቤተ መቅደስ ሊሠራለት የሚችል ማነው? በፊቱ ዕጣን የሚታጠንበትን እንጂ ቤተ መቅደስ እሠራለት ዘንድ እኔ ማን ነኝ?

7. “ስለዚህ አንተ በወርቅና በብር፣ በናስና በብረት፣ በሐምራዊና በደማቅ ቀይ፣ በሰማያዊም ግምጃ ሥራ ዕውቀት ያለውን እንዲሁም አባቴ ዳዊት ካዘጋጃቸው ከእኔ የእጅ ባለ ሙያዎች ጋር በይሁዳና በኢየሩሳሌም የቅርጻ ቅርጽ ጥበብ ሥራ የሚሠራ ሰው ላክልኝ።

8. ሰዎችህ ከሊባኖስ እንጨት በመቍረጥ ሥራ ዐዋቂዎች መሆናቸውን ስለማውቅ፣ ከሊባኖስ የዝግባ፣ የጥድና የሰንደል ዕንጨትም ላክልኝ፤ ሰዎቼም ከሰዎችህ ጋር አብረው ይሠራሉ።

9. የምሠራው ቤተ መቅደስ ትልቅና እጅግ ውብ መሆን ስላለበት፣ ብዙ ጠርብ ያዘጋጁልኛልና።

10. ዕንጨቱን ለሚቈርጡ አገልጋዮችህ ሃያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ ዱቄት፣ ሃያ ሺህ የባዶስ መስፈሪያ ወይን ጠጅና ሃያ ሺህ የባዶስ መስፈሪያ ዘይት እሰጣለሁ።”

11. የጢሮስ ንጉሥ ኪራምም ለሰሎሞን እንዲህ ሲል በደብዳቤ መለሰለት፤“እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለሚወድድ አንተን በእነርሱ ላይ አነገሠህ፤”

12. ኪራምም በመቀጠል እንዲህ አለ፤“ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ! ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስን፣ ለራሱም ቤተ መንግሥትን የሚሠራ፣ ብልኅነትንና ማስተዋልን የተሞላ ጥበበኛ ልጅ ለንጉሥ ዳዊት ሰጥቶአልና።

13. “እጅግ ብልሃተኛ የሆነውን ኪራም አቢን ልኬልሃለሁ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 2