ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 19:5-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. በምድሪቱም ላይ በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች ሁሉ ዳኞችን ሾመ፤

6. እንዲህም አላቸው፤ “እናንተ የምትፈርዱት ለሰው ሳይሆን፣ ፍርድ በምትሰጡበት ጊዜ ሁሉ ከእናንተ ጋር ለሆነው ለእግዚአብሔር ስለ ሆነ፣ በምትሰጡት ውሳኔ ሁሉ ብርቱ ጥንቃቄ አድርጉ፤

7. አሁንም እግዚአብሔርን መፍራት በእናንተ ላይ ይሁን፤ በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ ፍርድ ማጣመም፣ አድልዎ ማድረግና መማለጃ መቀበል ስለሌለ ተጠንቅቃችሁ ፍረዱ።”

8. ኢዮሣፍጥም በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔርን ሕግ እንዲያስፈጽሙና ለሚነሡ ክርክሮችም እልባት እንዲሰጡ ከሌዋውያን፣ ከካህናትና ከእስራኤል ቤትአለቆች ጥቂት ሰዎች ሾመ፤ እነርሱም መኖሪያቸው በኢየሩሳሌም ሆነ።

9. እነርሱንም እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፤ “እግዚአብሔርን በመፍራት፣ በታማኝነትና በፍጹም ልብ አገልግሉ።

10. በየከተማው ከሚኖሩት ወገኖቻችሁ ስለ ደም መፋሰስ ወይም ሕግን፣ ትእዛዛትን፣ ደንብንና ሥርዐትን ስለ መተላለፍ በሚቀርብላችሁ በማናቸውም ጒዳይ እግዚአብሔርን እንዳይበድሉ አስጠንቅቋቸው፤ ያለዚያ ግን ቊጣው በእናንተና በወንድሞቻችሁ ላይ ይመጣል፤ ይህን ብታደርጉ በደለኞች አትሆኑም።

11. “የእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ላይ የካህናቱ አለቃ አማርያ፣ የንጉሡ በሆነው ነገር ሁሉ ላይ የይሁዳ ነገድ መሪ የሆነው የእስማኤል ልጅ ዝባድያ በላያችሁ ተሾመዋል፤ ሌዋውያኑ ደግሞ በፊታችሁ አለቆች ሆነው ያገለግላሉ፤ በርትታችሁ ሥሩ፤ እግዚአብሔርም መልካም ከሚያደርጉ ጋር ይሁን።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 19