ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 18:23-34 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

23. ከዚያም የክንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ወጥቶ ሚካያን በጥፊ መታውና፣ “ለመሆኑ የእግዚአብሔር መንፈስ አንተን ያነጋገረህ፣ በየት በኩል አልፎኝ ነው?” አለው።

24. ሚካያም፣ “ለመሸሸግ ወደ እልፍኝህ በምትሄድበት በዚያ ዕለት ታገኘዋለህ” አለው።

25. ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “ሚካያን ይዛችሁ ወደ ከተማዪቱ ገዥ ወደ አሞንና ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ ላኩት፤

26. እነርሱንም፣ ‘ንጉሡ፣ ይህን ሰው እስር ቤት አስገቡት፤ በደህና እስክመለስም ድረስ ከደረቅ ቂጣና ከውሃ በስተቀር ምንም አትስጡት ብሎአል’ በሏቸው።”

27. ሚካያም፣ “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረም ማለት ነው!” አለ፤ ቀጥሎም፣ “እናንተ ሰዎች ሁላችሁ ስሙኝ” አለ።

28. ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ገለዓድ ወጡ።

29. የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “እኔ ልብሴን ለውጬ ወደ ጦርነቱ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ሌላ ሰው መስሎ ወደ ጦርነቱ ገባ።

30. በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ የሠረገላ አዛዦቹን፣ “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር፣ ትንሽም ሆነ ትልቅ ከሌላ ከማንም ጋር አትዋጉ” ብሎ አዘዛቸው።

31. የሠረገላው አዛዦችም ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፣ “የእስራኤል ንጉሥ ይህ ነው” ብለው አሰቡ፤ ሊወጉትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ረዳው፤ አምላክም ከእርሱ መለሳቸው፤

32. የሠረገላ አዛዦቹም የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን በተረዱ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ።

33. ይሁን እንጂ ቀስቱን በነሲብ ቢያስፈነጥረው በጥሩሩ መጋጠሚያዎች መካከል አልፎ የእስራኤልን ንጉሥ ወጋው። ንጉሡም ሠረገላ ነጂውን “ተመለስና ከጦርነቱ አውጣኝ፤ ቈስያለሁና” አለው።

34. ጦርነቱ ቀኑን ሙሉ እንደ ተፋፋመዋለ፤ የእስራኤልም ንጉሥ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ እስከ ምሽት ድረስ ተደግፎ ነበር፤ ፀሓይ ስትጠልቅም ሞተ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 18