ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 15:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የእግዚአብሔር መንፈስ በዖዴድ ልጅ በአዛርያስ ላይ መጣ።

2. እርሱም አሳን ሊገናኘው ወጣ፤ እንዲህም አለው፤ አሳ፣ እናንተም ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ፤ አድምጡኝ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር ስትሆኑ፣ እርሱም ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ብትፈልጉት ይገኝላችኋል፤ ብትተውት ግን፣ ይተዋችኋል።

3. እስራኤል ያለ እውነተኛ አምላክ፣ ያለ አስተማሪ ካህንና ያለ ሕግ ብዙ ዘመን አሳልፈዋል።

4. በመከራቸው ጊዜ ግን፣ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው ፈለጉት፤ እርሱም ተገኘላቸው።

5. በዚያን ዘመን በምድር ነዋሪዎች ሁሉ ዘንድ ታላቅ ሁከት ስለ ነበር፣ በሰላም ወጥቶ መግባት አስተማማኝ አልነበረም።

6. እግዚአብሔር በተለያየ መከራ ያስጨንቃቸው ስለ ነበር፣ አንዱ መንግሥት በሌላው መንግሥት፣ አንዱም ከተማ በሌላው ከተማ ይደመሰስ ነበር።

7. እናንተ ግን የድካማችሁን ዋጋ ስለምታገኙ በርቱ፤ እጃችሁም አይላላ።”

8. አሳ ይህን ቃልና የነቢዩን የዖዴድን ልጅ የዓዛርያስን ትንቢት በሰማ ጊዜ በረታ። ከመላው ይሁዳና ከብንያም ምድር፣ በኤፍሬምም ኰረብታዎች ላይ ከያዛቸው ከተሞች አስጸያፊዎቹን ጣዖታት አስወገደ። ከእግዚአብሔር መቅደስ ሰበሰብ ፊት ለፊት የነበረውንም የእግዚአብሔር መሠዊያ አደሰ።

9. አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር መሆኑን ባዩ ጊዜ፣ ከእስራኤል ብዙ ሰዎች እርሱን ተጠግተው ነበር፤ እርሱም ይሁዳንና ብንያምን እንዲሁም ከኤፍሬም፣ ከምናሴና ከስምዖን መጥተው ከእነርሱ ጋር የተቀመጡትን ሰበሰበ።

10. እነርሱም በአሳ ዘመነ መንግሥት በዐሥራ አምስተኛው ዓመት፣ በሦስተኛው ወር በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ።

11. በዚያን ጊዜ በምርኮ ካመጡት ውስጥ ሰባት መቶ በሬ፣ ሰባት ሺ በግና ፍየል ለእግዚአብሔር ሠዉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 15