ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 1:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበር፣ እጅግም ስላገነነው፣ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በመንግሥቱ ላይ ተደላድሎ ተቀመጠ።

2. ከዚያም ሰሎሞን ለመላው እስራኤል፣ ለሻለቆች፣ ለመቶ አለቆች፣ ለዳኞች፣ ለእስራኤል መሪዎች ሁሉ እንዲሁም ለየቤተ ሰቡ አለቆች ተናገረ።

3. የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የአምላክ የመገናኛ ድንኳን በዚያ ስለ ነበር፣ ሰሎሞንና መላው ጉባኤ በገባዖን ወዳለው ኰረብታ ሄዱ።

4. በዚያ ጊዜ ዳዊት የአምላክን ታቦት ከቂሪያት ይዓሪም በኢየሩሳሌም ድንኳን ተክሎ ወዳዘጋጀለት ስፍራ አምጥቶት ነበር፤

5. ይሁን እንጂ የሆር ልጅ፣ የኡሪ ልጅ ባስልኤል የሠራው መሠዊያ በገባዖን በእግዚአብሔር ማደሪያ ድንኳን ፊት ለፊት ይገኝ ነበር፤ ስለዚህ ሰሎሞንና ጉባኤው ይህንኑ ፈለጉ።

6. ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ወዳለው ወደ ናሱ መሠዊያ ወጥቶ በላዩ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።

7. በዚያ ሌሊት እግዚአብሔር ለሰሎሞን ተገልጦ፣ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ሁሉ ጠይቀኝ” አለው።

8. ሰሎሞን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ለአባቴ ለዳዊት ታላቅ በጎነት አድርገህለታል፤ እኔንም በእግሩ ተክተህ አንግሠኸኛል።

9. አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ያነገሥኸኝ ብዛቱ እንደ ትቢያ በሆነ ሕዝብ ላይ ስለ ሆነ፣ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው ተስፋ ይጽና።

10. ይህን ሕዝብ ለመምራት እንድችል፣ ጥበብና ዕውቀትን ስጠኝ፤ ይህ ካልሆነ ይህን ታላቅ ሕዝብህን ማን ሊገዛ ይችላል?”

11. እግዚአብሔርም ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “የልብህ መሻት ይህ ስለ ሆነ፣ ብልጥግናና ሀብት ወይም የጠላቶችህን ነፍስ ወይም ረጅም ዕድሜ ስላልጠየቅህ፣ ነገር ግን ባነገሥሁህ ሕዝቤ ላይ የምትገዛበትን ጥበብና ዕውቀት ስለ ጠየቅህ፣

12. ጥበብና ዕውቀት ይሰጥሃል፤ እንዲሁም ከአንተ በፊት የነበረ ማንኛውም ንጉሥ ያላገኘውን፣ ከአንተ በኋላም የሚነሣው የማያገኘውን ብልጽግና፣ ሀብትና ክብር እሰጥሃለሁ።”

13. ሰሎሞንም የመገናኛው ድንኳን ካለበት ከገባዖን ኰረብታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 1