ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 8:14-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ከዚያም አዛሄል ከኤልሳዕ ዘንድ ወጥቶ ወደ ጌታው ተመለሰ፤ ቤንሀዳድም፣ “ለመሆኑ ኤልሳዕ ምን አለህ?” ሲል ጠየቀው፤ አዛሄልም፣ “በርግጥ ከበሽታህ እንደምትድን ነግሮኛል” አለው።

15. በማግስቱ ግን ወፍራም ልብስ ወስዶ በውሃ ከነከረ በኋላ የንጉሡን ፊት ሸፈነው፤ ንጉሡም በዚሁ ሞተ፤ ከዚያም አዛሄል በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

16. የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት፣ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮሆራም በይሁዳ ነገሠ።

17. እርሱም ሲነግሥ ዕድሜው ሠላሳ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ስምንት ዓመት ገዛ።

18. ያገባት የአክዓብ ልጅ ስለ ነበረች የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም የእስራኤልን ነገሥታት መንገድ ተከተለ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

19. ይሁን እንጂ ስለ ባሪያው ስለ ዳዊት ሲል፣ እግዚአብሔር ይሁዳን ሊያጠፋ አልፈለገም፤ ምክንያቱም ለዳዊትና ለዘሩ መብራት እንደማያሳጣ ተስፋ ሰጥቶ ነበርና።

20. በኢዮሆራም ዘመነ መንግሥት፣ ኤዶምያስ በይሁዳ ላይ ዐምፆ የራሱን ንጉሥ አነገሠ።

21. ስለዚህም ኢዮሆራም ሠረገሎቹን ሁሉ አሰልፎ ወደ ጸዒር ዘመተ። ኤዶማውያንም እርሱንና የሠረገላ አዛዦቹን ከበቡ፤ እርሱና የሠረገላ አዛዦቹ ግን በሌሊት ተነሥተው ከበባውን ጥሰው ወጡ፤ ሰራዊቱም ሸሽቶ ተመለሰ።

22. ኤዶምያስም እስከ ዛሬ ድረስ በይሁዳ ላይ እንደ ዐመፀ ነው፤ ልብናም በዚሁ ጊዜ ዐምፆ ነበር።

23. በኢዮሆራም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

24. ኢዮሆራምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ እንደ እነርሱም ሁሉ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ አካዝያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

25. የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ የኢዮሆራም ልጅ አካዝያስ በይሁዳ ነገሠ።

26. አካዝያስ ሲነግሥ ዕድሜው ሀያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አንድ ዓመት ገዛ። እናቱ ጎቶልያ ትባላለች፤ እርሷም የእስራኤል ንጉሥ የዖምሪ የልጅ ልጅ ነበረች።

27. አካዝያስ ከአክዓብ ቤተ ሰብ ጋር በጋብቻ የተሳሰረ ስለ ነበር፣ የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በአክዓብ ቤት መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ።

28. አካዝያስም ከአክዓብ ልጅ ከኢዮራም ጋር ሆኖ በሶርያ ንጉሥ በአዛሄል ላይ ለመዝመት ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሄደ፤ ሶርያውያንም በዚያ ኢዮራምን አቈሰሉት።

29. ስለዚህ ንጉሥ ኢዮራም፣ በሬማት ከአዛሄል ጋር ባደረገው ጦርነት ሶርያውያን ካደረሱበት ቊስል ለማገገም ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ።ከዚያም የአክዓብ ልጅ ኢዮራም ስለ ታመመ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራሆም ልጅ አካዝያስ ሊጠይቀው ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 8