ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 8:10-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ኤልሳዕም፣ “ሂድና፣ ‘መዳኑንስ በርግጥ ትድናለህ’ በለው፤ ነገር ግን እንደሚሞት እግዚአብሔር ገልጦልኛል” ሲል መለሰለት።

11. እስኪያፍር ድረስም፣ አዛሄልን ትኵር ብሎ ተመለከተው፤ ከዚያም የእግዚአብሔር ሰው እንባውን አፈሰሰ።

12. አዛሄልም፣ “ጌታዬ የሚያለቅሰው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።ኤልሳዕም መልሶ፣ “በእስራኤላውያን ላይ የምታደርሰውን ጒዳት ስለማውቅ ነው፤ ምሽጎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ጐልማሶቻቸውን በሰይፍ ትገድላለህ፤ ሕፃናታቸውን በምድር ላይ ትፈጠፍጣለህ፤ ያረገዙ ሴቶቻቸውንም ሆድ ትቀድዳለህ” አለው።

13. አዛሄልም፣ “ለመሆኑ እንደ ውሻ የሚቈጠር አገልጋይህ ይህን ጀብዱ መፈጸም እንዴት ይችላል?” አለ።ኤልሳዕም መልሶ፣ “መቼም አንተ በሶርያ ላይ እንደምትነግሥ እግዚአብሔር አሳይቶኛል” አለው።

14. ከዚያም አዛሄል ከኤልሳዕ ዘንድ ወጥቶ ወደ ጌታው ተመለሰ፤ ቤንሀዳድም፣ “ለመሆኑ ኤልሳዕ ምን አለህ?” ሲል ጠየቀው፤ አዛሄልም፣ “በርግጥ ከበሽታህ እንደምትድን ነግሮኛል” አለው።

15. በማግስቱ ግን ወፍራም ልብስ ወስዶ በውሃ ከነከረ በኋላ የንጉሡን ፊት ሸፈነው፤ ንጉሡም በዚሁ ሞተ፤ ከዚያም አዛሄል በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

16. የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት፣ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮሆራም በይሁዳ ነገሠ።

17. እርሱም ሲነግሥ ዕድሜው ሠላሳ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ስምንት ዓመት ገዛ።

18. ያገባት የአክዓብ ልጅ ስለ ነበረች የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም የእስራኤልን ነገሥታት መንገድ ተከተለ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

19. ይሁን እንጂ ስለ ባሪያው ስለ ዳዊት ሲል፣ እግዚአብሔር ይሁዳን ሊያጠፋ አልፈለገም፤ ምክንያቱም ለዳዊትና ለዘሩ መብራት እንደማያሳጣ ተስፋ ሰጥቶ ነበርና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 8