ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 7:2-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ንጉሡ በክንዱ ላይ የተደገፈውም የጦር አለቃ፣ የእግዚአብሔርን ሰው፣ “እንዲያው ለመሆኑ፣ እግዚአብሔር የሰማያትን መስኮቶች ቢከፍት እንኳ ይህ ሊሆን ይችላልን?” ሲል ጠየቀው።ኤልሳዕም፣ “ይህን አንተው ራስህ በዐይንህ ታየዋለህ፤ ይሁን እንጂ ከዚያ አንዳች አትቀምስም” አለው።

3. በዚህ ጊዜ የሚያሠቅቅ የቆዳ በሽታ የያዛቸው አራት ሰዎች በከተማዪቱ መግቢያ በር አጠገብ ነበሩ፤ እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “እስክንሞት ድረስ በዚህ የምንቆየው ለምንድን ነው?

4. ታዲያ፣ ‘ወደ ከተማዪቱ እንግባ ብንል’ በዚያም ራብ ስላለ እንሞታለን፤ በዚሁም ብንሆን ያው መሞታችን እንደሁ አልቀረም፤ ስለዚህ ወደ ሶርያውያኑ ሰፈር ዝም ብለን እንሂድ፤ ዝም ካሉን ሕይወታችን ትተርፋለች፤ ከገደሉንም ያው ሞቶ መገላገል ነው።”

5. ከዚያም መሸትሸት ሲል ተነሥተው ወደ ሶርያውያን ሰፈር ሄዱ፤ ወደ ሰፈሩ ጥግ ሲደርሱም አንድም ሰው በዚያ አልነበረም።

6. ይህ የሆነበትም ምክንያት እግዚአብሔር የሠረገሎችንና የፈረሶችን እንዲሁም የብዙ ሰራዊት ድምፅ ሶርያውያን እንዲሰሙ አድርጎ ስለ ነበር ነው፤ እርስ በእርሳቸው፣ “እነሆ፣ የእስራኤል ንጉሥ በእኛ ላይ አደጋ ለመጣል፣ የኬጢያውያንንና የግብፃውያንን ነገሥታት ቀጥሮ አምጥቶብናል” ተባባሉ።

7. ከዚያም መሸትሸት ሲል ተነሥተው ሸሹ፤ ድንኳኖቻቸውን፣ ፈረሶቻቸውንና አህዮቻቸውንም አልወሰዱም ነፍሳቸውን ብቻ ለማዳን ሲሉ ሰፈሩን እንዲሁ እንዳለ ትተው ሄዱ።

8. ለምጽ ያለባቸውም ሰዎች ወደ ሰፈሩ አጠገብ ከደረሱ በኋላ፣ ከድንኳኖቹ ወደ አንዱ ገብተው በሉ፤ ጠጡም፤ ከዚያም ብር፣ ወርቅና ልብስ ይዘው በመሄድ ደበቁት። ተመልሰው በመምጣትም ወደ ሌላው ድንኳን ገብተው ሌሎች ነገሮችን በመውሰድ እንደዚሁ ደበቁ።

9. እርስ በርሳቸውም፣ “ያደረግነው ትክክል አይደለም፤ ዕለቱ የምሥራች ቀን ነው፤ እኛ ግን የራሳችን ብቻ አደረግነው፤ እስኪነጋም ከቈየን በደለኞች እንሆናለን፤ ስለዚህ ወደ ቤተ መንግሥት በፍጥነት ሄደን እንንገር” ተባባሉ።

10. ስለዚህ ሄደው የከተማዪቱን መግቢያ በር ጠባቂዎች ጮኸው በመጥራት፣ “ወደ ሶርያውያን ሰፈር ገባን፤ እዚያም ከታሰሩ ፈረሶችና አህዮች በቀር አንድም ሰው አልነበረም፤ የማንም ድምፅ አልተሰማም፤ ድንኳኖቹም እንዳሉ ናቸው” ብለው ነገሯአቸው።

11. የበሩ ጠባቂዎችም ይህንኑ አስተጋቡ፤ ዜናውም በቤተ መንግሥቱ ተሰማ።

12. ንጉሡም በሌሊት ተነሥቶ ለጦር አለቆቹ እንዲህ አላቸው፤ “ሶርያውያን ያደረጉብንን እነግራችኋለሁ፤ መራባችንን ስለሚያውቁ፣ ‘መቼም መውጣታቸው አይቀርም፤ ከዚያም ከነሕይወታቸው እንማርካቸዋለን፤ እኛም ሰተት ብለን ወደ ከተማዪቱ እንገባለን’ በማለት በገጠር ለመደበቅ ከሰፈራቸው ወጥተዋል።”

13. ከጦር አለቆቹም አንዱ እንዲህ አለ፤ “ጥቂት ሰዎች በከተማዪቱ ውስጥ ከተረፉት ፈረሶች አምስቱን ይዘው ይሂዱ፤ ዕጣ ፈንታቸውም በዚህ ከቀሩት እስራኤላውያን ሁሉ ዕድል ጋር አንድ ነው፤ የሚጠብቃቸው ቢኖር በዚህ በሙሉ እንዳለቁት እስራኤላውያን መሆን ብቻ ነው፤ ስለዚህ እንላካቸውና የሆነውን እንይ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 7