ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 7:12-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ንጉሡም በሌሊት ተነሥቶ ለጦር አለቆቹ እንዲህ አላቸው፤ “ሶርያውያን ያደረጉብንን እነግራችኋለሁ፤ መራባችንን ስለሚያውቁ፣ ‘መቼም መውጣታቸው አይቀርም፤ ከዚያም ከነሕይወታቸው እንማርካቸዋለን፤ እኛም ሰተት ብለን ወደ ከተማዪቱ እንገባለን’ በማለት በገጠር ለመደበቅ ከሰፈራቸው ወጥተዋል።”

13. ከጦር አለቆቹም አንዱ እንዲህ አለ፤ “ጥቂት ሰዎች በከተማዪቱ ውስጥ ከተረፉት ፈረሶች አምስቱን ይዘው ይሂዱ፤ ዕጣ ፈንታቸውም በዚህ ከቀሩት እስራኤላውያን ሁሉ ዕድል ጋር አንድ ነው፤ የሚጠብቃቸው ቢኖር በዚህ በሙሉ እንዳለቁት እስራኤላውያን መሆን ብቻ ነው፤ ስለዚህ እንላካቸውና የሆነውን እንይ።”

14. ስለዚህ ሁለት ሠረገሎች ከነፈረሶቻቸው መረጡ፤ ንጉሡም፣ “ሂዱና የሆነውን ነገር እዩ” ብሎ ከሶርያውያን ሰራዊት በኋላ እንዲሄዱ ላካቸው።

15. እነርሱም እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ተከተሏቸው። ሶርያውያን በጥድፊያ ሲሸሹ፣ የጣሉትንም ልብስና ዕቃ በየመንገዱ ላይ ተበታትኖ አገኙ፤ መልክተኞቹም ተመልሰው ይህንኑ ለንጉሡ ነገሩት።

16. ከዚያም ሕዝቡ ወጥቶ የሶርያውያንን ሰፈር በዘበዘ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው አንድ መስፈሪያ ማለፊያ ዱቄት በአንድ ሰቅል፣ ሁለት መስፈሪያ ገብስም በአንድ ሰቅል ተሸጠ።

17. በዚህ ጊዜ ንጉሡ እጁን ይደግፈው የነበረውን የጦር አለቃ፣ የቅጥሩ በር ኀላፊ አድርጎት ነበርና በበራፉ መተላለፊያ ላይ ሕዝቡ ሲጋፋ ረጋገጠው፤ ያ የእግዚአብሔር ሰው ንጉሡ ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ አስቀድሞ እንደ ተናገረውም የጦር አለቃው ሞተ።

18. እንዲሁም የእግዚአብሔር ሰው ለንጉሡ፣ “ነገ በዚሁ ሰዓት በሰማርያ በር ላይ አንድ መስፈሪያ ዱቄት በአንድ ሰቅል፣ ሁለት መስፈሪያ ገብስም በአንድ ሰቅል ይሸጣል” ያለውም ተፈጸመ።

19. የጦር አለቃው ለእግዚአብሔር ሰው፣ “እግዚአብሔር የሰማይን መስኮቶች ቢከፍት እንኳ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ብሎት ስለ ነበር፣ የእግዚአብሔር ሰው፣ “ይህን አንተው ራስህ ታያለህ፤ ከዚህ ግን አንዳች አትበላም” ሲል መልሶለት ነበር።

20. በበሩ መተላለፊያ ላይ ሕዝቡ ረጋግጦት ስለ ሞተም፣ የተነገረበት በትክክል ደረሰ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 7