ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 6:25-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

25. ከተማዪቱን እንደ ከበባትም የአንድ አህያ ጭንቅላት በሰማኒያ ሰቅል ብር፣ የጎሞር አንድ ስምንተኛ የርግብ ኵስ በአምስት ሰቅል ብር እስኪ ሸጥ ድረስ ታላቅ ራብ ሆነ።

26. የእስራኤልም ንጉሥ በቅጥሩ ላይ በሚመላለስበት ጊዜ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “ጌታዬ፣ ንጉሥ ሆይ፤ እባክህ ርዳኝ!” አለች።

27. ንጉሡም፣ “እግዚአብሔር ካልረዳሽ እኔ እንዴት ልረዳሽ እችላለሁ? ከዐውድማው ነው ወይስ ከወይን መጥመቂያው የምረዳሽ?” ሲል መለሰላት።

28. ከዚያም፣ “ለመሆኑ ችግርሽ ምንድ ነው?” ሲል ጠየቃት።እርሷም እንዲህ ስትል መለሰችለት፤ “ይህች ሴት፣ ‘ዛሬ እንድንበላው ልጅሽን አምጪው፤ ነገ ደግሞ የእኔን ልጅ እንበላዋለን’ አለችኝ።

29. ስለዚህ ልጄን ቀቅለን በላነው። በማግሥቱም፣ ‘እንድንበላው ልጅሽን አምጪው’ አልኋት፤ እርሷ ግን ደበቀችው።”

30. ንጉሡም ሴቲቱ ያለችውን ሲሰማ ልብሱን ቀደደ፤ በቅጥሩ ላይ በሚመላለስበትም ጊዜ በውስጥ ማቅ መልበሱን ሕዝቡ አየ።

31. ንጉሡም፣ “የሣፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ራስ ዛሬ በዐንገቱ ላይ ካደረ፣ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፤ ከዚህም የባሰ ያምጣብኝ” ብሎ ዛተ።

32. በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ በቤቱ ተቀምጦ ነበር፤ ሽማግሌዎችም አብረውት ተቀምጠው ነበር። ንጉሡም መልእክተኛ ቀድሞት እንዲሄድ አደረገ። የተላከውም ሰው ከመድረሱ በፊት ኤልሳዕ ለሽማግሌዎቹ፣ “ይህ ነፍሰ ገዳይ ራሴን ለመቊረጥ ሰው መላኩን ታያላችሁ? እነሆ፤ አሁንም መልእክተኛው ሲደርስ በሩን ዘግታችሁ እንዳይገባ አድርጉ። የጌታው የእግሩ ኮቴ ከኋላው ይሰማ የለምን?” አላቸው።

33. ኤልሳዕ ከሽማግሌዎቹ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለም፣ መልእክተኛው ወደ እርሱ ወረደ። ንጉሡም ደርሶ፣ “ይህ ጥፋት የመጣው ከእግዚአብሔር ነው፤ ታዲያ እኔ ከእግዚአብሔር ምን እጠብቃለሁ?” አለ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 6