ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 6:14-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ስለዚህ ፈረሶችና ሠረገሎች እንዲሁም ብዙ ሰራዊት ወደዚያ ላከ። እነርሱም በሌሊት ደርሰው ከተማዪቱን ከበቡ።

15. የእግዚአብሔር ሰው አገልጋይ በማለዳ ተነሥቶ ወደ ውጭ ሲወጣ፣ በፈረሶችና በሠረገሎች የተጠናከረ ሰራዊት ከተማዪቱን ከቧት ነበር። አገልጋዩም “ጌታዬ ሆይ፤ ምን ማድረግ ይሻለናል?” ሲል ጠየቀ።

16. ነቢዩም፣ “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ” አለው።

17. ኤልሳዕም፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ያይ ዘንድ እባክህ ዐይኖቹን ክፈትለት” ብሎ ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የአገልጋዩን ዐይኖች ከፈተለት፤ ሲመለከትም፤ የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ ተራራውን ሞልተውት አየ።

18. ሶርያውያንም ወርደው ወደ እርሱ ሲመጡ ኤልሳዕ፣ “ይህን ሕዝብ ዕውር አድርገው” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ስለዚህ ኤልሳዕ በጠየቀው መሠረት እግዚአብሔር ዕውር አደረጋቸው።

19. ኤልሳዕም፣ “መንገዱ በዚህ አይደለም፤ ከተማዪቱም ይህች አይደለችም፤ ወደምት ፈልጉት ሰው መርቼ እንዳደርሳችሁም እኔን ተከተሉኝ” አላቸው። ከዚያም መርቶ ወደ ሰማርያ ወሰዳቸው።

20. ወደ ከተማዪቱም ከገቡ በኋላ ኤልሳዕ፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዲያዩ የእነዚህን ሰዎች ዐይን ክፈት” አለ። እግዚአብሔርም ዐይኖቻቸውን ከፈተ። እነርሱም በሰማርያ ውስጥ መሆናቸውን አዩ።

21. የእስራኤልም ንጉሥ ባያቸው ጊዜ፣ “አባቴ ሆይ፤ ልግደላቸውን? ልፍጃቸውን?” ብሎ ኤልሳዕን ጠየቀው።

22. እርሱም፣ “አትግደላቸው፤ ለመሆኑ በሰይፍህና በቀስትህ የማረክሃቸውን ትገድላቸው ዘንድ ይገባሃልን? አሁንም የሚበሉትንና የሚጠጡትን አስቀርብላቸው፤ በልተው ጠጥተውም ወደ ጌታቸውም ይሂዱ” አለው።

23. ስለዚህ ታላቅ ግብዣ አዘጋጅቶላቸው ከበሉና ከጠጡ በኋላ አሰናብቶአቸው ወደ ጌታቸው ሄዱ። የሶርያ አደጋ ጣዮችም የእስራኤልን ምድር ለመውረር ከዚያ በኋላ አልተመለሱም።

24. ከጥቂት ጊዜ በኋላም የሶርያ ንጉሥ ቤን ሐዳድ ሰራዊቱን ሁሉ ሰበሰበ፤ ወጥቶም ሰማርያን ከበባት።

25. ከተማዪቱን እንደ ከበባትም የአንድ አህያ ጭንቅላት በሰማኒያ ሰቅል ብር፣ የጎሞር አንድ ስምንተኛ የርግብ ኵስ በአምስት ሰቅል ብር እስኪ ሸጥ ድረስ ታላቅ ራብ ሆነ።

26. የእስራኤልም ንጉሥ በቅጥሩ ላይ በሚመላለስበት ጊዜ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “ጌታዬ፣ ንጉሥ ሆይ፤ እባክህ ርዳኝ!” አለች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 6