ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 6:13-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ንጉሡም፣ “ሰዎች ልኬ እንዳስይዘው፣ የት እንደሚገኝ ፈልጉ” ሲል አዘዘ። ከዚያም፣ “በዶታይን ይገኛል” የሚል ዜና ደረሰው።

14. ስለዚህ ፈረሶችና ሠረገሎች እንዲሁም ብዙ ሰራዊት ወደዚያ ላከ። እነርሱም በሌሊት ደርሰው ከተማዪቱን ከበቡ።

15. የእግዚአብሔር ሰው አገልጋይ በማለዳ ተነሥቶ ወደ ውጭ ሲወጣ፣ በፈረሶችና በሠረገሎች የተጠናከረ ሰራዊት ከተማዪቱን ከቧት ነበር። አገልጋዩም “ጌታዬ ሆይ፤ ምን ማድረግ ይሻለናል?” ሲል ጠየቀ።

16. ነቢዩም፣ “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ” አለው።

17. ኤልሳዕም፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ያይ ዘንድ እባክህ ዐይኖቹን ክፈትለት” ብሎ ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የአገልጋዩን ዐይኖች ከፈተለት፤ ሲመለከትም፤ የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ ተራራውን ሞልተውት አየ።

18. ሶርያውያንም ወርደው ወደ እርሱ ሲመጡ ኤልሳዕ፣ “ይህን ሕዝብ ዕውር አድርገው” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ስለዚህ ኤልሳዕ በጠየቀው መሠረት እግዚአብሔር ዕውር አደረጋቸው።

19. ኤልሳዕም፣ “መንገዱ በዚህ አይደለም፤ ከተማዪቱም ይህች አይደለችም፤ ወደምት ፈልጉት ሰው መርቼ እንዳደርሳችሁም እኔን ተከተሉኝ” አላቸው። ከዚያም መርቶ ወደ ሰማርያ ወሰዳቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 6