ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 6:12-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ከጦር አለቆቹም አንዱ፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ ከእኛ በኩል ማንም ሰው የለም፤ ነገር ግን አንተ በእልፍኝህ ሆነህ እንኳ የምትናገረውን አንዲቱም ሳትቀር ለእስራኤል ንጉሥ የሚነግረው በእስራኤል ያለው ነቢዩ ኤልሳዕ ነው” አለው።

13. ንጉሡም፣ “ሰዎች ልኬ እንዳስይዘው፣ የት እንደሚገኝ ፈልጉ” ሲል አዘዘ። ከዚያም፣ “በዶታይን ይገኛል” የሚል ዜና ደረሰው።

14. ስለዚህ ፈረሶችና ሠረገሎች እንዲሁም ብዙ ሰራዊት ወደዚያ ላከ። እነርሱም በሌሊት ደርሰው ከተማዪቱን ከበቡ።

15. የእግዚአብሔር ሰው አገልጋይ በማለዳ ተነሥቶ ወደ ውጭ ሲወጣ፣ በፈረሶችና በሠረገሎች የተጠናከረ ሰራዊት ከተማዪቱን ከቧት ነበር። አገልጋዩም “ጌታዬ ሆይ፤ ምን ማድረግ ይሻለናል?” ሲል ጠየቀ።

16. ነቢዩም፣ “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ” አለው።

17. ኤልሳዕም፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ያይ ዘንድ እባክህ ዐይኖቹን ክፈትለት” ብሎ ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የአገልጋዩን ዐይኖች ከፈተለት፤ ሲመለከትም፤ የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ ተራራውን ሞልተውት አየ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 6