ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 5:17-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ንዕማንም እንዲህ አለው፤ “ስጦታውን የማትቀበል ከሆነ፣ ለማንኛውም አምላክ የሚቃጠል ወይም ሌላ መሥዋዕት ስለማላቀርብ፣ ሁለት የበቅሎ ጭነት ዐፈር እንድወስድ ትፈቅድልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።

18. ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ አንድ ነገር ብቻ አገልጋይህን ይቅር ይበለው፤ ይኸውም ጌታዬ ለመስገድ ወደ ሬሞን ቤተ ጣዖት በሚገባበት ጊዜ ክንዴን ሲደገፍ እኔም እንደ እርሱ በዚያ ብሰግድ፣ በሬሞን ቤተ ጣዖት በመስገዴ እግዚአብሔር አገልጋይህን ይቅር ይበለው።”

19. ኤልሳዕም፣ “በሰላም ሂድ” አለው። ንዕማን ጥቂት ራቅ ብሎ እንደሄደ፣

20. የእግዚአብሔር ሰው አገልጋይ ግያዝ፣ “ጌታዬ፣ ይህ ሶርያዊ ንዕማን ያመጣውን አለመቀበሉ ደግም አይደል፤ ሕያው እግዚአብሔርን! ተከትዬ ሄጄ ከእርሱ አንድ ነገር ማግኘት አለብኝ” ብሎ አሰበ።

21. ስለዚህ ግያዝ ንዕማንን ተከተለው፤ ንዕማንም ግያዝ እየሮጠ ወደ እርሱ መምጣቱን ባየ ጊዜ፣ ሊገናኘው ከሠረገላው ወርዶ፣ “ምነው፤ በደኅና መጣህን?” ሲል ጠየቀው።

22. ግያዝም፣ “ሁሉም ደኅና ነው፤ ግን ጌታዬ፣ ‘ከነቢያት ማኅበር ሁለት ወጣቶች ከኰረብታማው አገር ከኤፍሬም ወደ እኔ አሁን በድንገት ስለመጡ፣ ‘እባክህ አንድ መክሊት ብርና ሁለት ሙሉ ልብስ ስጣቸው ብለህ ንገር’ ብሎ ልኮኛል’ አለው።

23. ንዕማንም፣ “እባክህ ሁለት መክሊት ውሰድ” በማለት ግያዝን አስጨንቆ ለመነው። ከዚያም ሁለቱን መክሊት ብር፣ በሁለት ከረጢት ውስጥ አስሮ ሁለት ሙሉ ልብስ ጨምሮ ለሁለት አገልጋዮቹ አስያዘ፤ እነርሱም ያን ተሸክመው ከግያዝ ፊት ፊት ሄዱ።

24. ግያዝም ወደ ኰረብታው እንደ ደረሰ፣ ዕቃዎቹን ከአገልጋዮቹ ተቀብሎ በቤቱ ውስጥ አስቀመጠ፤ ሰዎቹንም አሰናብቶአቸው ሄዱ።

25. ከዚያም ገብቶ በጌታው በኤልሳዕ ፊት ቆመ።ኤልሳዕም፣ “ግያዝ ሆይ፤ የት ነበርህ?” ሲል ጠየቀው።ግያዝም፣ “አገልጋይህ የትም አልሄደም” ብሎ መለሰ።

26. ኤልሳዕ ግን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰው ሊገናኝህ ከሠረገላው ሲወርድ መንፈሴ ከአንተ ጋር አልሄደምን? እንዲያው ለመሆኑ ጊዜው ገንዘብና ልብስ፣ የወይራ ዘይት ተክልና የወይን ተክል ቦታ፣ የበግና የከብት መንጋ፣ ወንድና ሴት አገልጋይ የሚቀበሉበት ነውን?

27. ስለዚህ የንዕማን ለምጽ በአንተ ላይ ይጣበቃል፤ ለዘላለምም ወደ ዘርህ ይተላለፋል።” ከዚያም ግያዝ ከኤልሳዕ ፊት ወጣ፤ እንደ በረዶ እስኪነጣም ድረስ ለምጻም ሆኖ ወጣ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 5