ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 4:11-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. አንድ ቀን ኤልሳዕ ወደዚያው መጥቶ ወደ ማረፊያ ክፍሉ በመውጣት ጋደም አለ።

12. አገልጋዩን ግያዝንም፣ “ሱነማዪቱን ጥራት” አለው፤ በጠራትም ጊዜ መጥታ በፊቱ ቆመች።

13. ኤልሳዕም፣ “ ‘ለእኛ ስትይ በጣም ተቸግረሻል፣ ምን እንዲደረግልሽ ትፈልጊአለሽ? ለንጉሡ ወይስ ለሰራዊቱ አዛዥ የምንነግርልሽ ጒዳይ አለን?’ ብለህ ጠይቃት” አለው።ሴቲቱም መልሳ፣ “እኔ እኮ የምኖረው በገዛ ወገኖቼ መካከል ነው” አለችው።

14. ኤልሳዕም፣ “ታዲያ ምን ይደረግላት” ሲል ጠየቀ።ግያዝም፣ “ልጅ እኮ የላትም፤ ባሏም ሸምግሎአል” አለ።

15. ኤልሳዕም፣ “በል እንግዲያው ጥራት” አለው፤ እርሱም ጠርቶአት መጥታ እበራፉ ላይ ቆመች።

16. ኤልሳዕም የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ ወንድ ልጅ ትታቀፊያለሽ” አላት፤እርሷም፣ “አይደለም ጌታዬ፣ አንተ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፤ ኋላ አገልጋይህን መዋሸት እንዳይሆንብህ!” አለችው።

17. ሴትዮዋም ፀነሰች፤ ኤልሳዕ እንደ ነገራትም በተባለው ጊዜ ወንድ ልጅ ወለደች።

18. ሕፃኑ አደገ፤ አንድ ቀንም አባቱ ከዐጫጆች ጋር ወደነበረበት ቦታ ሄደ።

19. አባቱንም፣ “ራሴን! ራሴን!” አለው። አባቱም አገልጋዩን፣ “ተሸክመህ ወደ እናቱ አድር ሰው” አለው።

20. አገልጋዩም አንሥቶ እናቱ ዘንድ አደረሰው፤ ልጁም እስከ እኩለ ቀን ድረስ በእናቱ ጭን ላይ ተቀመጠ፤ ከዚያም ሞተ።

21. ወደ ላይ ወጥታም በእግዚአብሔር ሰው ዐልጋ ላይ አስተኛችው፤ በሩንም ዘግታበት ወጣች።

22. ከዚያም ባሏን ጠርታ፣ “ወደ እግዚአብሔር ሰው በፍጥነት ደርሼ እንድመለስ አንድ አገልጋይና አንድ አህያ ላክልኝ” አለችው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 4