ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 3:8-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ኢዮሣፍጥም፣ “የምንዘምተው በየትኛው መንገድ ነው” ብሎ ጠየቀው፤ኢዮራምም “በኤዶም ምድረ በዳ አልፈን ነው” ሲል መለሰለት።

9. ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ከይሁዳ ንጉሥና ከኤዶም ንጉሥ ጋር ለመዝመት ተነሣ። ሰባት ቀን ከዞሩም በኋላ ለሰራዊቱም ሆነ ለእንስሶቻቸው የተረፈ ውሃ አልነበረም።

10. የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ወዮ! እግዚአብሔር እኛን ሦስት ነገሥታት የጠራን ለሞዓብ አሳልፎ ሊሰጠን ነውን?” አለ።

11. ኢዮሣፍጥ ግን፣ “በእርሱ አማካይነት እግዚአብሔርን ለመጠየቅ እንድንችል፣ የእግዚአብሔር ነቢይ እዚህ የለምን?” በማለት ጠየቀ።ከእስራኤል ንጉሥ የጦር አለቆችም አንዱ፣ “ቀድሞ የኤልያስን እጅ ያስታጥብ የነበረው፤ የሣፋጥ ልጅ ኤልሳዕ በዚህ አለ” ብሎ መለሰለት።

12. ኢዮሣፍጥም፣ “የእግዚአብሔር ቃል ከእርሱ ዘንድ ይገኛል” አለ፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ፣ ኢዮሣፍጥና የኤዶም ንጉሥ አብረው ወደ እርሱ ወረዱ።

13. ኤልሳዕም የእስራኤልን ንጉሥ፤ “ከአንተ ጋር ምን የሚያገናኘን ጒዳይ አለና መጣህ፤ አሁን የአባትህና የእናትህ ነቢያት ወዳሉበት ሂድ” አለው።የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ፣ “ይህማ አይሆንም፤ በሞዓብ እጅ አሳልፎ ሊሰጠን እኛን ሦስት ነገሥታት አንድ ላይ የጠራን እግዚአብሔር ነው” አለ።

14. ኤልሳዕም እንዲህ አለው፤ “የማገለግለው ሕያው እግዚአብሔርን፣ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ባላከብር ኖሮ፣ አንተን አላይም ወይም ጒዳዬ አልልህም ነበር።

15. አሁንም ባለ በገና አምጡልኝ።”ታዲያ ባለ በገናው በሚደረድርበት ጊዜ፣ የእግዚአብሔር እጅ በኤልሳዕ ላይ መጣ፤

16. እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔር የሚለው እንዲህ ነው፤ ‘በዚህ ሸለቆ ብዙ ጒድጓዶች ቈፍሩ።

17. እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘ነፋስም ሆነ ዝናብ አታዩም፤ ሸለቆው ግን በውሃ ይሞላል፤ እናንተ፣ የቀንድ ከብቶቻችሁና ሌሎች እንስሶቻችሁም ትጠጣላችሁ።

18. ይህ በእግዚአብሔር ፊት ቀላል ነገር ነው። ሞዓብንም በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋል።

19. የተመሸጉትን ከተሞችና ያማሩትን ከተሞቻቸውን ሁሉ ድል ታደርጋላችሁ። ውብ ዛፎቻቸውን ሁሉ ትቈርጣላችሁ፤ ምንጮቻቸውን በሙሉ ትደፍናላችሁ፤ መልካሙንም ዕርሻ በድንጋይ ታበላሹታላችሁ።”

20. በማግስቱ መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ፣ እነሆ፤ ከኤዶም በኩል ውሃ እየጐረፈ መጣ፤ ምድሪቱም ውሃ በውሃ ሆነች።

21. በዚህ ጊዜ ነገሥታቱ ሊወጓቸው መምጣታቸውን ሞዓባውያን ሁሉ ሰምተው ነበርና፣ ልጅም ሆነ ሽማግሌ፣ መሣሪያ መያዝ የቻለ ሁሉ ተጠርቶ በመውጣት በጠረፉ ላይ ይጠባበቅ ጀመር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 3