ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 25:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር መላ ሰራዊቱን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ዘመተ፤ ከከተማዪቱ ቅጥር ውጭ ሰፈረ፤ ዙሪያውንም በሙሉ በዕርድ ከበባት።

2. ከተማዪቱም እስከ ሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት ዐሥራ አንደኛ ዓመት ድረስ እንዲሁ እንደ ተከበበች ቈየች።

3. በአራተኛው ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማዪቱ ውስጥ የተከሠተው ራብ ጸንቶ ስለ ነበር ሕዝቡ የሚቀምሰው አጣ።

4. ምንም እንኳ ባቢሎናውያን ከተማዪቱን እንደ ከበቧት ቢሆንም የከተማዪቱ ቅጥር ተጣሰ፤ ሰራዊቱም ሁሉ በንጉሡ አትክልት አጠገብ ባሉት በሁለቱ ቅጥሮች መካከል በሚገኘው በር አልፎ በሌሊት ሸሸ፤ ሽሽቱም ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ ነበር።

5. ይሁን እንጂ የባቢሎን ሰራዊት ንጉሡን ተከታትሎ በኢያሪኮ ሜዳ ላይ ደረሰበት። ወታደሮቹ ሁሉ ተለይተውት ተበታትነው ነበር።

6. እርሱም ተያዘ፤ በዚያን ጊዜ ሪብላ ወደ ነበረው ወደ ባቢሎን ንጉሥ አመጡት፤ ቅጣትም ተፈረደበት።

7. ሴዴቅያስ ዐይኑ እያየም የገዛ ልጆቹን ገደሉበት፤ ከዚያም ሁለት ዐይኖቹን በማውጣት በናስ ሰንሰለት አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 25