ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 21:11-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. “የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ይህን ሁሉ አስጸያፊ ኀጢአት ሠርቶአል፤ ከእርሱ በፊት ከነበሩት አሞራውያን ይልቅ ክፉ ድርጊት ፈጽሞአል፤ ይሁዳንም በጣዖታቱ አስቶአል።

12. ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘ለሚሰማ ሁሉ ጆሮዎቹ ጭው እንዲሉ የሚያደርግ ክፉ መከራ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ አመጣለሁ።

13. በሰማርያ ላይ ያዘጋጀሁትን መለኪያ ገመድ፣ የአክዓብንም ቤት የለካሁበትን ቱንቢ በኢየሩሳሌም ላይ እዘረጋለሁ፤ አንድ ሰው ሳሕን እንደ ሚወለውል ከወለወለም በኋላ እንደሚገለብጠው እኔም ኢየሩሳሌምን ወልውዬ እገለብጣታለሁ።

14. የርስቴንም ቅሬታ እተዋቸዋለሁ፤ ለጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ለጠላቶቻቸውም ሁሉ ብዝበዛና ምርኮ ይሆናሉ።

15. ይህን የማደርገውም የቀድሞ አባቶቻቸው ከግብፅ ምድር ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ በፊቴ ክፉ ድርጊት ስለፈጸሙና ለቊጣ ስላነሣሡኝ ነው።”

16. ይልቁንም ምናሴ፣ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት እንዲፈጽም ይሁዳን ካሳተበት ኀጢአት ሌላ፣ ኢየሩሳሌምን ከዳር እስከ ዳር እስኪሞላት ድረስ ብዙ ንጹሕ ደም አፈሰሰ።

17. በምናሴ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የሠራውን ኀጢአት ጨምሮ የፈጸመው ድርጊት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

18. ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ “የዖዛ አትክልት” በሚባለው በቤተ መንግሥቱ አትክልት ውስጥ ተቀበረ። ልጁ አሞንም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

19. አሞን ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሁለት ዓመት ገዛ፤ እናቱ ሜሶላም ትባላለች፤ እርሷም የዮጥባ አገር ሰው የሐሩስ ልጅ ነበረች።

20. አባቱ ምናሴ እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

21. አባቱ በሄደበት መንገድ ሁሉ ሄደ፤ አባቱ ያመለካቸውን አማልክት አመለከ፤ ሰገደላቸውም።

22. የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ተወ፤ በእግዚአብሔርም መንገድ አልሄደም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 21