ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 18:8-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. እስከ ጋዛና እስከ ግዛቷ ዳርቻ በመዝለቅ ፍልስጤማውያንን ከመጠበቂያ ማማ እስከ ተመሸገችው ከተማ ድረስ ድል አደረጋቸው።

9. ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ የእስራኤልም ንጉሥ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ወደ ሰማርያ ገሥግሦ ከተማዪቱን ከበባት፤

10. በሦስተኛውም ዓመት መጨረሻ ያዛት። ሰማርያ የተያዘችውም ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት፣ ሆሴዕ በእስ ራኤል ላይ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ነበር።

11. የአሦር ንጉሥ እስራኤልን ማርኮ ወደ አሦር በማፍለስ በአላሔ፣ በጎዛን ውስጥ በአቦር ወንዝ አጠገብና በሜዶን ከተሞች አሰፈራቸው።

12. ይህ የደረሰባቸውም የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ከመስማት ይልቅ ኪዳኑን ስላፈረሱ ነበር፤ ትእዛዞቹን አላደመጡም፤ ደግሞም አልፈጸሙም።

13. ሕዝቅያስ በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም የተመሸጉትን የይሁዳን ከተሞች ሁሉ አደጋ ጥሎ ያዛቸው።

14. ስለዚህ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ “በደለኛው እኔ ነኝ፤ ተመለስልኝ፤ እኔም የምትጠይቀኝን ሁሉ እከፍላለሁ፤” ሲል በለኪሶ ወደ ሰፈረው ወደ አሦር ንጉሥ ይህን መልእክት ላከ። የአሦርም ንጉሥ፣ የይሁዳን ንጉሥ ሕዝቅያስን ሦስት መቶ መክሊት ብርና ሠላሳ መክሊት ወርቅ እንዲያገባለት ጠየቀው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 18