ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 16:8-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. አካዝም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤቶች የሚገኘውን ብርና ወርቅ አውጥቶ ለአሦር ንጉሥ ገጸ በረከት ላከለት።

9. የአሦር ንጉሥም፣ የአካዝን ልመና በመቀበል፤ ደማስቆን አጥቅቶ ያዛት፤ ሕዝቧን ማርኮ ወደ ቂር አፈለሳቸው፤ ረአሶንንም ገደለው።

10. ከዚያም ንጉሥ አካዝ የአሦርን ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶርን ለመገናኘት ወደ ደማስቆ ሄደ። በደማስቆም ያለውን መሠዊያ አይቶ፣ ንድፉን ከዝርዝር ጥናቱ ጋር ለካህኑ ለኦርያ ላከለት።

11. ካህኑ ኦርያም ንጉሥ አካዝ ከደማስቆ በላከለት ዝርዝር ጥናት መሠረት መሠዊያ ሠራ፤ ንጉሡ አካዝ ከመመለሱም በፊት አጠናቀቀው።

12. ንጉሡ ከደማስቆ ተመልሶ በመጣ ጊዜ፣ መሠዊያውን አየ፤ ቀርቦም በመሠዊያው ላይ ወጣ፤

13. ከዚያም የሚቃጠል መሥዋዕቱንና የእህል ቊርባኑን በመሠዊያው ላይ አቀረበ፤ የመጠጥ ቊርባኑን አፈሰሰ፤ የኅብረት መሥዋዕቱንም ደም በመሠዊያው ላይ ረጨ።

14. በአዲሱ መሠዊያና በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መካከል፣ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ የነበረውን የናስ መሠዊያ፣ ከቦታው አሥነስቶ ከአዲሱ መሠዊያ በስተ ሰሜን በኩል አኖረው።

15. ከዚያም ንጉሥ አካዝ፣ ካህኑን ኦርያን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “በዚህ በትልቁ አዲስ መሠዊያ ላይ የጧቱን የሚቃጠል መሥዋዕትና የማታውን የእህል ቊርባን፣ የንጉሡን የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህሉን ቊርባን እንዲሁም የመላውን የአገሪቱን ሕዝብ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የእህልና የመጠጥ ቊርባናቸውን አቅርብ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ደምና የሌላውን መሥዋዕት ደም ሁሉ በመሠዊያው ላይ እርጨው፤ የናሱ መሠዊያ ግን እኔ መመሪያ ለመጠየቅ የምጠቀምበት ይሆናል።”

16. ካህኑ ኦርያም ንጉሡ አካዝ እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።

17. ንጉሡ አካዝም የጐንና የጐን ሳንቃዎቹን ነቅሎ ወሰደ፤ በተንቀሳቃሹ መቆሚያ ላይ ያሉትን የመታጠቢያ ሳሕኖች አስወገደ። የውሃ ማጠራቀሚያውን ክብ ገንዳ ከታች ተሸክመው ከያዙት ከዐሥራ ሁለቱ የናስ ቅርጽ ኮርማዎች ላይ አውርዶ በጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ አስቀመጠው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 16