ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 14:9-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ግን ለይሁዳ ንጉሥ ለአሜስያስ እንዲህ ሲል ላከበት፤ “አንድ የሊባኖስ ኵርንችት፣ ለአንድ የሊባኖስ ዝግባ፣ ‘ሴት ልጅህን ለልጄ በሚስትነት ስጠው’ አለው፤ ከዚያም አንድ የሊባኖስ ዱር አውሬ መጥቶ ኵርንችቱን በእግሩ ረገጠው።

10. በእርግጥ ኤዶምን ድል አድርገሃል፤ ታዲያ ልብህ አለመጠን አይኵራራ። ድል በማድረግህ አትንጠራራ፤ አርፈህ ተቀመጥ! ጠብ በመጫር የራስህንስ፣ የይሁዳንስ ውድቀት ለምን ትሻለህ?”

11. አሜስያስ ግን አልሰማም፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ወጣ፤ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ምድር በቤትሳሚስ ፊት ለፊት ጦርነት ገጠሙ።

12. ይሁዳ በእስራኤል ድል ሆነ፤ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ።

13. የእስራኤል ንጉሥ ዮአስም የአካዝያስን የልጅ ልጅ፣ የኢዮአስን ልጅ የይሁዳን ንጉሥ አሜስያስን ቤትሳሚስ ላይ ማረከው። ከዚያም ዮአስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፤ ከኤፍሬም ቅጥር በር አንሥቶ የማእዘን ቅጥር በር እስከተባለው ድረስ ርዝመቱ አራት መቶ ክንድ የሆነውን ቅጥር አፈረሰ።

14. በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤቶች ያለውን ወርቅና ብር በሙሉ በዚያም የተገኘውን ዕቃ ሁሉ በመውሰድ ምርኮኞችንም ይዞ ወደ ሰማርያ ተመለሰ።

15. በዮአስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር፣ ያደረገውና የፈጸመው ሁሉ በይሁዳ ንጉሥ በአሜስያስ ላይ ያደረገው ጦርነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

16. ዮአስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ፤ ልጁ ኢዮርብዓምም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

17. የኢዮአስ ልጅ የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ ከሞተ በኋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ።

18. በአሜስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

19. አሜስያስ በኢየሩሳሌም ሴራ ስለጠነሰሱበት ሸሽቶ ወደ ላኪሶ ሄደ፤ እነርሱ ግን የሚከታተሉት ሰዎች ወደዚያው ልከው አስገደሉት፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 14