ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 1:8-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. እነርሱም “ሰውየው ጠጒራም ልብስ የለበሰ ነው፤ በወገቡም ላይ ጠፍር ታጥቆአል” አሉት።ንጉሡም፣ “ዐወቅሁት፤ ቴስብያዊው ኤልያስ ነው” አላቸው።

9. ከዚያም ንጉሡ አንድ የአምሳ አለቃ ከአምሳ ወታደሮቹ ጋር ወደ ኤልያስ ላከ። የአምሳ አለቃውም ኤልያስ ወደ ተቀመጠበት ኰረብታ ጫፍ ወጥቶ፣ “አንተ የእግዚአብሔር ሰው፤ ንጉሡ፣ ‘ና ውረድ’ ይልሃል” አለው።

10. ኤልያስም መልሶ የአምሳ አለቃውን፣ “እኔ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንሁ፣ እሳት ከሰማይ ወርዳ፣ አንተንና አምሳውን ሰዎችህን ትብላ!” አለው። ከዚያም እሳት ከሰማይ ወርዳ የአምሳ አለቃውንና ሰዎቹን ፈጽማ በላች።

11. እንደ ገናም ንጉሡ ሌላ የአምሳ አለቃ ከአምሳ ሰዎቹ ጋር ላከ፤ የአምሳ አለቃውም፣ “አንተ የእግዚአብሔር ሰው፤ ንጉሡ፣ ‘አሁኑኑ ና ውረድ’ ይልሃል” አለው።

12. ኤልያስም መልሶ፣ “እኔ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንሁ እሳት ከሰማይ ወርዳ አንተንና ሃምሳውን ሰዎችህን ትብላ!” አለው፤ ከዚያም እሳት ከሰማይ ወርዳ እርሱንና ሰዎቹን ፈጽማ በላች።

13. ስለዚህም ንጉሡ ሦስተኛውን የአምሳ አለቃ ከአምሳ ሰዎቹ ጋር ላከ። ይህም ሦስተኛው የአምሳ አለቃ ወጥቶ፣ በኤልያስ ፊት በጒልበቱ ተንበርክኮ እንዲህ ሲል ለመነ፤ “አንተ የእግዚአብሔር ሰው፤ እባክህ የእኔና የእነዚህ የአምሳዎቹ አገልጋዮችህ ነፍስ በፊትህ የከበረች ትሁን።

14. እነሆ፤ እሳት ከሰማይ ወርዳ፣ የፊተኞቹን ሁለት አምሳ አለቆችና ሰዎቻቸውን ሁሉ በላች፤ አሁን ግን ሕይወቴ በፊትህ የከበረች ትሁን።”

15. የእግዚአብሔርም መልአክ ኤልያስን፣ “አብረኸው ውረድ፤ ደግሞም አትፍራው” አለው። ስለዚህ ኤልያስ ተነሣ፤ አብሮትም ወደ ንጉሡ ወረደ።

16. ንጉሡንም፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ለመሆኑ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ስለ ራስህ ለመጠየቅ መልእክተኞች የላክኸው በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነውን? ይህን በማድረግህም ከተኛህበት ዐልጋ ፈጽሞ አትነሣም፤ በርግጥ ትሞታለህ’ ” ብሎ ነገረው።

17. ስለዚህ አካዝያስ ኤልያስ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ሞተ።አካዝያስ ወንድ ልጅ ስላልነበረው፣ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም በይሁዳ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ወንድሙ ኢዮራም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

18. ሌላው አካዝያስ በዘመኑ ያከናወናቸውና የፈጸማቸው ሥራዎች ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ የተጻፉ አይደለምን?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 1