ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 3:17-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. አበኔር ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ተመካከረ፤ እንዲህም አለ፤ “ባለፈው ጊዜ ዳዊት በላያችሁ እንዲነግሥ ፈልጋችሁ ነበር፤

18. እግዚአብሔር ለዳዊት፣ ‘በባሪያዬ በዳዊት ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅና ከጠላቶቻቸው እጅ እታደጋቸዋለሁ’ ብሎ ተስፋ ስለ ሰጠው፣ ይህን አሁኑኑ አድርጉት።”

19. እንዲሁም አበኔር ለብንያማውያን ራሱ ሄዶ ይህንኑ ነገራቸው፤ ከዚያም እስራኤልና መላው የብንያም ቤት ለማድረግ የፈለጉትን ሁሉ ለዳዊት ለመንገር ወደ ኬብሮን ሄደ።

20. አበኔር ከሃያ ሰዎች ጋር ዳዊት ወዳለበት ወደ ኬብሮን መጣ፤ ዳዊትም ለአበኔርና አብረውት ለነበሩት ሰዎች ግብዣ አደረገላቸው።

21. ከዚያም አበኔር ዳዊትን፤ “ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እንዲያደርጉ፣ ልብህ እንደተመኘውም ሁሉን እንድትገዛ ፈጥኜ ሄጄ፣ ለጌታዬ ለንጉሡ መላውን እስራኤልን ልሰብስብ” አለው። ስለዚህ ዳዊት አበኔርን አሰናበተው፤ በሰላምም ሄደ።

22. የዳዊትና የኢዮአብ ሰዎች በዚያኑ ጊዜ ብዙ ምርኮ ይዘው ከዘመቻ ተመለሱ። አበኔር ግን ዳዊት በሰላም አሰናብቶት ስለሄደ፣ በኬብሮን አልነበረም።

23. ኢዮአብና አብሮት የነበረው ሰራዊት ሁሉ እዚያ እንደ ደረሱ፣ የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሡ መምጣቱን፣ ንጉሡ እንዳሰናበተውና እርሱም በሰላም እንደሄደ፣ ኢዮአብ ሰማ።

24. ስለዚህ ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ገብቶ እንዲህ አለ፤ “ምን ማድረግህ ነው? እነሆ አበኔር መጥቶልህ እንዴት በሰላም እንዲሄድ አሰናበትኸው?

25. የኔርን ልጅ አበኔርን ታውቀዋለህ፤ የመጣው ሊያታልልህ፣ መውጣት መግባትህን ለማወቅና የምታደርገውን ሁሉ ሊሰልል ነው።”

26. ከዚያም ኢዮአብ ከዳዊት ዘንድ ወጣ፤ አበኔርን እንዲያመጡትም መልክተኞች ላከ፤ መልክተኞቹም ከሴይር የውሃ ጒድጓድ አጠገብ መለሱት። ዳዊት ግን ይህን አላወቀም ነበር።

27. አበኔር ወደ ኬብሮን በተመለሰ ጊዜ፣ ኢዮአብ በቈይታ የሚያነጋግረው በመምሰል ዞር አድርጎ ወደ ቅጽሩ በር ይዞት ሄደ፤ እዚያም የወንድሙን የአሣሄልን ደም ለመበቀል ሲል፣ ሆዱ ላይ ወግቶ ገደለው።

28. ዳዊት ይህን ነገር ቈይቶ በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “እኔም ሆንሁ መንግሥቴ ከኔር ልጅ ከአበኔር ደም በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ንጹሕ ነን፤

29. ደሙ በኢዮአብ ራስና በአባቱ ቤት ሁሉ ላይ ይሁን፤ ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ወይም አሠቃቂ የቈዳ በሽታ ያለበት፣ በምርኵዝ የሚሄድ አንካሳ፣ ወይም በሰይፍ ተመቶ የሚወድቅ ወይም የሚበላው ያጣራብተኛ ከኢዮአብ ቤት አይታጣ።”

30. አበኔር ገባዖን ላይ በተደረገው ጦርነት የኢዮአብንና የአቢሳን ወንድም አሣሄልን ገድሎት ስለ ነበር፣ እነርሱም አበኔርን ገደሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 3