ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 3:13-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ዳዊትም፣ “ይሁን እሺ፣ ከአንተ ጋር ስምምነቱን አደርጋለሁ፣ ነገር ግን ከአንተ አንዲት ነገር እሻለሁ፤ ይኸውም ወደ እኔ ስትመጣ በመጀመሪያ የሳኦልን ሴት ልጅ ሜልኮልን ይዘህልኝ እንድትመጣ ነው፤ ያለዚያ ግን ወደ እኔ እንዳትመጣ” አለ።

14. ከዚያም ዳዊት፣ “የመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ማጫ የከፈልሁባትን ሚስቴን ሜልኮልን ስጠኝ” ብሎ ወደ ሳኦል ልጅ ወደ ኢያቡስቴ መልክተኞች ላከበት።

15. ስለዚህም ኢያቡስቴ መልክተኛ ልኮ፣ ሜልኮልን ከባሏ ከሌሳ ልጅ ከፈልጢኤል ወሰዳት።

16. ባሏም እስከ ብራቂም ከተማ ድረስ እያለቀሰ ተከትሎአት ሄደ፤ ከዚያም አበኔር፣ “በል በቃል! ወደ ቤትህ ተመለስ” አለው። ስለዚህም ተመለሰ።

17. አበኔር ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ተመካከረ፤ እንዲህም አለ፤ “ባለፈው ጊዜ ዳዊት በላያችሁ እንዲነግሥ ፈልጋችሁ ነበር፤

18. እግዚአብሔር ለዳዊት፣ ‘በባሪያዬ በዳዊት ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅና ከጠላቶቻቸው እጅ እታደጋቸዋለሁ’ ብሎ ተስፋ ስለ ሰጠው፣ ይህን አሁኑኑ አድርጉት።”

19. እንዲሁም አበኔር ለብንያማውያን ራሱ ሄዶ ይህንኑ ነገራቸው፤ ከዚያም እስራኤልና መላው የብንያም ቤት ለማድረግ የፈለጉትን ሁሉ ለዳዊት ለመንገር ወደ ኬብሮን ሄደ።

20. አበኔር ከሃያ ሰዎች ጋር ዳዊት ወዳለበት ወደ ኬብሮን መጣ፤ ዳዊትም ለአበኔርና አብረውት ለነበሩት ሰዎች ግብዣ አደረገላቸው።

21. ከዚያም አበኔር ዳዊትን፤ “ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እንዲያደርጉ፣ ልብህ እንደተመኘውም ሁሉን እንድትገዛ ፈጥኜ ሄጄ፣ ለጌታዬ ለንጉሡ መላውን እስራኤልን ልሰብስብ” አለው። ስለዚህ ዳዊት አበኔርን አሰናበተው፤ በሰላምም ሄደ።

22. የዳዊትና የኢዮአብ ሰዎች በዚያኑ ጊዜ ብዙ ምርኮ ይዘው ከዘመቻ ተመለሱ። አበኔር ግን ዳዊት በሰላም አሰናብቶት ስለሄደ፣ በኬብሮን አልነበረም።

23. ኢዮአብና አብሮት የነበረው ሰራዊት ሁሉ እዚያ እንደ ደረሱ፣ የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሡ መምጣቱን፣ ንጉሡ እንዳሰናበተውና እርሱም በሰላም እንደሄደ፣ ኢዮአብ ሰማ።

24. ስለዚህ ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ገብቶ እንዲህ አለ፤ “ምን ማድረግህ ነው? እነሆ አበኔር መጥቶልህ እንዴት በሰላም እንዲሄድ አሰናበትኸው?

25. የኔርን ልጅ አበኔርን ታውቀዋለህ፤ የመጣው ሊያታልልህ፣ መውጣት መግባትህን ለማወቅና የምታደርገውን ሁሉ ሊሰልል ነው።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 3