ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 2:4-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. የይሁዳም ሰዎች ወደ ኬብሮን መጡ፤ በዚያም ዳዊትን ቀብተው በይሁዳ ቤት ላይ አነገሡት።ሳኦልን የቀበሩት የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች መሆናቸውን ለዳዊት በነገሩት ጊዜ፣

5. እርሱም የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ይህን እንዲነግሩ መልእክተኞች ላከ፤ “በእንዲህ ዐይነት ሁኔታ ጌታችሁን ሳኦልን በመቅበር በጎነት አሳይ ታችኋልና እግዚአብሔር ይባርካችሁ፤

6. አሁንም እግዚአብሔር ጽኑ ፍቅሩንና ታማኝነቱን ይግለጥላችሁ፤ እናንተ ይህን ስላደረጋችሁ፣ እኔም እንደዚሁ በጎ ነገር አደርግላችኋለሁ፤

7. እንግዲህ ጠንክሩ፤ በርቱ ጌታችሁ ሳኦል ሞቶአልና፤ የይሁዳ ቤትም እኔን ቀብተው በላያቸው አንግሠውኛል።”

8. በዚህ ጊዜ የሳኦል ሰራዊት አዛዥ የኔር ልጅ አበኔር፣ የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ወደ መሃናይም አሻገረው፤

9. እርሱንም በገለዓድ፣ በአሴር፣ በኢይዝራኤል፣ በኤፍሬምና በብንያም እንዲሁም በእስራኤል ሁሉ ላይ አነገሠው።

10. የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ በእስራኤል ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበረ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ። የይሁዳ ቤት ግን ዳዊትን ተከተለ።

11. ዳዊት በኬብሮን ንጉሥ ሆኖ እስራኤልን የገዛው ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበረ።

12. የኔር ልጅ አበኔር፣ ከሳኦል ልጅ ከኢያቡስቴ አገልጋዮች ጋር ሆኖ ከመሃናይም ተነሥተው ወደ ገባዖን ሄዱ።

13. እነርሱንም የጽሩያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ሰዎች ወጥተው በገባዖን ኵሬ አጠገብ ተገናኟቸው፤ አንዱ ወገን በኵሬው ወዲህ ማዶ፣ ሌላው ወገን ደግሞ በኵሬው ወዲያ ማዶ ተቀመጠ።

14. ከዚያም አበኔር፣ ኢዮአብን፣ “ከእናንተም ከእኛም ጒልማሶች ይነሡና በፊታችን በጨበጣ ውጊያ ይጋጠሙ” አለው።ኢዮአብም፣ “ይሁን እሺ ይጋጠሙ” ብሎ መለሰ።

15. ስለዚህ ከብንያም ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ ዐሥራ ሁለት፣ ለዳዊት ደግሞ ዐሥራ ሁለት ሰዎች ተነሥተው ተቈጠሩ።

16. ከዚያም እያንዳንዱ ሰው የባለጋራውን ራስ በመያዝ ሰይፉን በጐኑ እየሻጠበት ተያይዘው ወደቁ። ስለዚህም በገባዖን የሚገኘው ያ ቦታ “የሰይፍ ምድር” ተባለ።

17. የዚያን ዕለቱ ጦርነት እጅግ ከባድ ነበር፤ አበኔርና የእስራኤል ሰዎች በዳዊት ሰዎች ድል ሆኑ።

18. ሦስቱ የጽሩያ ወንዶች ልጆች ኢዮአብ፣ አቢሳና አሣሄል እዚያው ነበሩ። አሣሄል እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበረ፤

19. ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ሳይል አበኔርን ተከታተለው።

20. አበኔርም ወደ ኋላው ዘወር ብሎ በመመልከት፣ “አሣሄል! አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፣ “አዎን እኔ ነኝ” ብሎ መለሰለት።

21. ከዚያም አበኔር፣ “ወደ ቀኝህ ወይም ወደ ግራህ ዘወር በልና አንዱን ጒልማሳ ይዘህ መሣሪያውን ንጠቀው” አለው። አሣሄል ግን እርሱን መከታተሉን አልተወም ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 2