ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 2:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚህ በኋላ ዳዊት፣ “ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን?” ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም፣ “አዎን ውጣ” አለው።ዳዊትም፣ “ወደ የትኛዪቱ ልሂድ?” ሲል ጠየቀ። እግዚአብሔርም፣ “ወደ ኬብሮን” ብሎ መለሰለት።

2. ስለዚህ ዳዊት ከሁለቱ ሚስቶቹ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ ጋር ወደዚያ ወጣ።

3. እንዲሁም ዳዊት አብረውት የነበሩትን ሰዎች ከነቤተ ሰቦቻቸው አመጣቸው፤ እነርሱም በኬብሮን ከተሞች ተቀመጡ።

4. የይሁዳም ሰዎች ወደ ኬብሮን መጡ፤ በዚያም ዳዊትን ቀብተው በይሁዳ ቤት ላይ አነገሡት።ሳኦልን የቀበሩት የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች መሆናቸውን ለዳዊት በነገሩት ጊዜ፣

5. እርሱም የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ይህን እንዲነግሩ መልእክተኞች ላከ፤ “በእንዲህ ዐይነት ሁኔታ ጌታችሁን ሳኦልን በመቅበር በጎነት አሳይ ታችኋልና እግዚአብሔር ይባርካችሁ፤

6. አሁንም እግዚአብሔር ጽኑ ፍቅሩንና ታማኝነቱን ይግለጥላችሁ፤ እናንተ ይህን ስላደረጋችሁ፣ እኔም እንደዚሁ በጎ ነገር አደርግላችኋለሁ፤

7. እንግዲህ ጠንክሩ፤ በርቱ ጌታችሁ ሳኦል ሞቶአልና፤ የይሁዳ ቤትም እኔን ቀብተው በላያቸው አንግሠውኛል።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 2