ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 19:16-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. የብራቂም ሰው የሆነው የጌራ ልጅ ብንያማዊው ሳሚ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ሆኖ ንጉሥ ዳዊትን ለመቀበል ፈጥኖ ወረደ።

17. ከእርሱም ጋር አንድ ሺህ ብንያማውያን፣ እንዲሁም የሳኦል ቤተ ሰብ አገልጋይ ሲባ ከዐሥራ አምስት ወንዶች ልጆቹና ከሃያ አሽከሮቹ ጋር ሆኖ አብረውት ነበሩ። ከዚያም ንጉሡ ወዳለበት ወደ ዮርዳኖስ በጥድፊያ ወረዱ።

18. የንጉሡን ቤተ ሰው ለማምጣትና እርሱ የሚፈልገውንም ሁሉ ለማድረግ በመልካው ተሻገሩ።የጌራ ልጅ ሳሚ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ በንጉሡም ፊት ተደፍቶ፣

19. እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ በደሌን አይቍጠርብኝ፤ ንጉሥ ጌታዬ ከኢየሩሳሌም በወጣህባት ዕለት የፈጸምሁትን ስሕተት እርሳው፤ ከአእምሮህም አውጣው።

20. እኔ አገልጋይህ ኀጢአት መሥራቴን አውቃለሁና፤ ዛሬ ግን ጌታዬን ንጉሡን ለመቀበል ከዮሴፍ ቤት ሁሉ የመጀመሪያ ሆኜ እነሆ መጥቻለሁ።”

21. ከዚያም የጽሩያ ልጅ አቢሳ፣ “ሳሚ በእግዚአብሔር የተቀባውን የረገመ ስለ ሆነ፣ መሞት አይገባውምን?” አለ።

22. ዳዊትም፣ “እናንት የጽሩያ ልጆች፣ እናንተንና እኔን ምን የሚያገናኘን ነገር አለ? ዛሬ ጠላት ሆናችሁኛል! ማንስ ቢሆን ዛሬ በእስራኤል ዘንድ ሰው መሞት አለበት? እኔ በእስራኤል ላይ ንጉሥ መሆኔን ያወቅሁበት ቀን አይደለምን?” ብሎ መለሰ።

23. ስለዚህ ንጉሡ ሳሚን፣ “አትሞትም” አለው፤ ይህንንም ንጉሡ በመሐላ አጸናለት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 19