ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 18:3-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ሰዎቹ ግን፣ “አንተ መውጣት የለብህም፤ እንድንሸሽ ብንገደድ፣ ሰዎቹ ከቁም ነገር አይቈጥሩንም፤ ግማሾቻችን እንኳ ብንሞት ደንታቸው አይደለም፣ አንተ ግን ብቻህን ከእኛ ከዐሥሩ ሺህ ትበልጣለህ፤ ስለዚህ በከተማ ሆነህ ብትረዳን ይሻላል” አሉት።

4. ንጉሡም፣ “መልካም መስሎ የታያችሁን ሁሉ አደርጋለሁ” አላቸው። ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ በመቶና በሺህ እየሆነ ተሰልፎ ሲወጣ፣ ንጉሡ በቅጥሩ በር ቆሞ ነበር።

5. ንጉሡም ኢዮአብን፣ አቢሳንና ኢታይን፣ “ለእኔ ስትሉ በወጣቱ ልጄ በአቤሴሎም ላይ ጒዳት እንዳታደርሱበት” ብሎ አዘዛቸው። ንጉሡ ልጁን አቤሴሎምን አስመልክቶ ለእያንዳንዱ አዛዥ ትእዛዝ ሲሰጥ ሰራዊቱ ሁሉ ሰማ።

6. ሰራዊቱ እስራኤልን ለመውጋት ተሰልፎ ወደ ሜዳ ወጣ፤ ጦርነቱም በኤፍሬም ደን ውስጥ ሆነ።

7. እዚያም የእስራኤል ሰራዊት በዳዊት ሰዎች ተመታ፤ በዚያም ቀን ታላቅ እልቂት ሆነ፤ ሃያ ሺህም ሰው ተገደለ።

8. ውጊያው በገጠሩ ሁሉ ተስፋፋ፤ በዚያን ቀን ሰይፍ ከጨረሰው ይልቅ ጫካ ውጦ ያስቀረው ሰው በለጠ።

9. በዚህ ጊዜ አቤሴሎም ከዳዊት ሰዎች ጋር ድንገት ተገናኘ፤ አቤሴሎም በበቅሎ ተቀምጦ ይሄድ ስለ ነበር፣ በቅሎዋ ጥቅጥቅ ያለ ቅርንጫፍ ባለው ትልቅ ወርካ ሥር በምታልፍበት ጊዜ፣ የአቤሴሎም ራስ በዛፉ ቅርንጫፍ ተያዘ፤ የተቀመጠበትም በቅሎ በሥሩ ስታልፍ፣ እርሱ በሰማይና በምድር መካከል ተንጠልጥሎ ቀረ።

10. አንድ ሰው ይህን አይቶ ለኢዮአብ፣ “እነሆ፤ አቤሴሎም በባሉጥ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ አየሁት” አለው።

11. ኢዮአብም ይህን የነገረውን ሰው፣ “ምን አልህ! ካየኸው ታዲያ ለምንድን ነው ያኔውኑ መተህ መሬት ላይ ያልጣልኸው? ይህን አድርገህ ቢሆን ኖሮ፣ ዐሥር ሰቅል ጥሬ ብርና የጀግና ሰው ቀበቶም እሸልምህ ነበር” አለው።

12. ሰውየው ግን እንዲህ አለ፤ “እኛ እየሰማን ንጉሡ፣ ‘ወጣቱ አቤሴሎም ጒዳት እንዳያገኘው ስለ እኔ ብላችሁ ጠብቁት’ ብሎ አንተን፣ አቢሳንና ኢታይን ያዘዛችሁ ስለ ሆነ፣ አንድ ሺህ ሰቅል ጥሬ ብር በእጄ ላይ ቢመዘንልኝ እንኳ፣ በንጉሡ ልጅ ላይ እጄን አላነሣም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 18