ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 16:6-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. የንጉሡ ወታደሮችና የክብር ዘቦቹ ሁሉ በዳዊት ግራና ቀኝ ቢኖሩም እንኳ፣ በዳዊትና በሹማምቱ ላይ ሁሉ ድንጋይ ይወረውርባቸው ነበር።

7. ሳሚም እንዲህ ብሎ ይራገም ነበር፤ “ውጣ! ከዚህ ውጣ! አንተ የደም ሰው፤ አንተ ክፉ ሰው፤

8. መንግሥቱን የወሰድክበትን የሳኦልን ቤተ ሰው ደም ሁሉ እግዚአብሔር ወደ አንተው እየመለሰው ነው። እግዚአብሔር መንግሥትህን ለልጅህ ለአቤሴሎም አሳልፎ ሰጥቶታል፤ አንተ የደም ሰው ስለ ሆንህ እነሆ፣ መከራ መጥቶብሃል።”

9. ከዚያም የጽሩያ ልጅ አቢሳ ንጉሡን፤ “ይህ የሞተ ውሻ፣ ንጉሥ ጌታዬን እንዴት ይራገማል? ልሻገርና ራሱን ልቍረጠው” አለ።

10. ንጉሡ ግን፣ “እናንት የጽሩያ ልጆች እናንተንና እኔን የሚያገናኘን ምን ነገር አለ? እግዚአብሔር፣ ‘ዳዊትን ርገመው’ ብሎት የሚረግመኝ ከሆነ፣ ‘ይህን ለምን አደረግህ’ ብሎ ማን ሊጠይቀው ይችላል?” አለው።

11. ከዚያም ዳዊት አቢሳንና ሹማምቱን ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “ከአብራኬ የወጣው ልጄ ሕይወቴን ሊያጠፋት ከፈለገ፣ ይህ ብንያማዊ ቢያደርገው ምን ያስደንቃል? ስለዚህ ተዉት፤ እግዚአብሔር በል ብሎት ነውና ይራገም፤

12. ምናልባትም እግዚአብሔር ሐዘኔን አይቶ በዛሬውም ርግማን ፈንታ በጎ ነገር ያደርግልኝ ይሆናል።”

13. ስለዚህም ዳዊትና ሰዎቹ መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ ሳሚም በአንጻሩ ባለው ኰረብታ ጥግ ጥግ እየሄደ ይራገም፣ ድንጋይ ይወረውርበትና ዐፈር ይበትንበት ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 16