ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 28:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ዳዊት በኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ የነገዱን የጦር አለቆች፣ ንጉሡን የሚያገለግሉትን የከፍለ ጦር አዛዦች፣ የሻለቆቹን፣ የመቶ አለቆቹን፣ የንጉሡና የልጆቹ ንብረትና ከብት ሁሉ ኀላፊ የሆኑትን፣ እንዲሁም የቤተ መንግሥቱን ሹማምት፣ ኀያላንና ጀግና ተዋጊዎቹን፣ በአጠቃላይ የእስራኤልን ሹማምት ሁሉ ጠራ።

2. ከዚያም ንጉሥ ዳዊት በእግሩ ቆሞ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞቼና ወገኖቼ ሆይ፤ እስቲ አድምጡኝ፤ ለእግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ ታቦት ማደሪያና ለአምላካችን እግር ማረፊያ የሚሆን ቤት ለመሥራት ዐስቤ ዕቅድ አውጥቼ ነበር።

3. እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ፤ ‘ጦረኛ ሰው ስለሆንህና ደምም ስላፈሰስህ፣ አንተ ለስሜ ቤት አትሠራም’።

4. “ነገር ግን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ለዘላለም እንድነግሥ ከቤተ ሰቤ ሁሉ እኔን መረጠ፤ መሪ እንዲሆንም ይሁዳን መረጠ፤ ከይሁዳም ቤት የእኔን ቤተ ሰብ መረጠ፤ ከአባቴ ልጆች መካከል ደግሞ በመላው እስራኤል ላይ እንድነግሥ ፈቃዱ ሆነ።

5. እግዚአብሔር ብዙ ልጆች ሰጥቶኛል፤ ከወንዶቹ ልጆቼ ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ዙፋን ላይ ተቀምጦ በእስራኤል ሁሉ ላይ እንዲነግሥ ደግሞ ልጄን ሰሎሞንን መርጦታል።

6. እንዲህም አለኝ፤ ‘ቤቴንና አደባባዮቼን የሚሠራልኝ ልጅህ ሰሎሞን ነው፤ ምክንያቱም ልጄ እንዲሆን መርጬዋለሁ፤ እኔም አባት እሆነዋለሁ።

7. አሁን እንደሚያደርገው ሁሉ፣ ትእዛዞቼንና ሕጎቼን ምንጊዜም ሳያወላውል የሚፈጽም ከሆነ፣ መንግሥቱን ለዘላለም አጸናታለሁ’።

8. “እንግዲህ አሁንም ይህቺን መልካሚቱን ምድር እንድትወርሱና ለልጆቻችሁም የዘላለም ርስት አድርጋችሁ እንድታወርሱአቸው፣ የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ ሁሉ በጥንቃቄ እንድታከብሩ በእስራኤል ሁሉ ፊት፣ በእግዚአብሔር ጉባኤና እግዚአብሔርም እየሰማ አዛችኋለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዜና መዋዕል 28