ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዳዊት ስለ ቤተ መቅደሱ ያወጣው ዕቅድ

1. ዳዊት በኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ የነገዱን የጦር አለቆች፣ ንጉሡን የሚያገለግሉትን የከፍለ ጦር አዛዦች፣ የሻለቆቹን፣ የመቶ አለቆቹን፣ የንጉሡና የልጆቹ ንብረትና ከብት ሁሉ ኀላፊ የሆኑትን፣ እንዲሁም የቤተ መንግሥቱን ሹማምት፣ ኀያላንና ጀግና ተዋጊዎቹን፣ በአጠቃላይ የእስራኤልን ሹማምት ሁሉ ጠራ።

2. ከዚያም ንጉሥ ዳዊት በእግሩ ቆሞ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞቼና ወገኖቼ ሆይ፤ እስቲ አድምጡኝ፤ ለእግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ ታቦት ማደሪያና ለአምላካችን እግር ማረፊያ የሚሆን ቤት ለመሥራት ዐስቤ ዕቅድ አውጥቼ ነበር።

3. እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ፤ ‘ጦረኛ ሰው ስለሆንህና ደምም ስላፈሰስህ፣ አንተ ለስሜ ቤት አትሠራም’።

4. “ነገር ግን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ለዘላለም እንድነግሥ ከቤተ ሰቤ ሁሉ እኔን መረጠ፤ መሪ እንዲሆንም ይሁዳን መረጠ፤ ከይሁዳም ቤት የእኔን ቤተ ሰብ መረጠ፤ ከአባቴ ልጆች መካከል ደግሞ በመላው እስራኤል ላይ እንድነግሥ ፈቃዱ ሆነ።

5. እግዚአብሔር ብዙ ልጆች ሰጥቶኛል፤ ከወንዶቹ ልጆቼ ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ዙፋን ላይ ተቀምጦ በእስራኤል ሁሉ ላይ እንዲነግሥ ደግሞ ልጄን ሰሎሞንን መርጦታል።

6. እንዲህም አለኝ፤ ‘ቤቴንና አደባባዮቼን የሚሠራልኝ ልጅህ ሰሎሞን ነው፤ ምክንያቱም ልጄ እንዲሆን መርጬዋለሁ፤ እኔም አባት እሆነዋለሁ።

7. አሁን እንደሚያደርገው ሁሉ፣ ትእዛዞቼንና ሕጎቼን ምንጊዜም ሳያወላውል የሚፈጽም ከሆነ፣ መንግሥቱን ለዘላለም አጸናታለሁ’።

8. “እንግዲህ አሁንም ይህቺን መልካሚቱን ምድር እንድትወርሱና ለልጆቻችሁም የዘላለም ርስት አድርጋችሁ እንድታወርሱአቸው፣ የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ ሁሉ በጥንቃቄ እንድታከብሩ በእስራኤል ሁሉ ፊት፣ በእግዚአብሔር ጉባኤና እግዚአብሔርም እየሰማ አዛችኋለሁ።

9. “አንተም ልጄ ሰሎሞን ሆይ፤ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ስለሚመረምርና ሐሳብን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ የአባትህን አምላክ ዕወቅ፤ በፍጹም ልብና በበጎ ፈቃድ አገልግለው። ከፈለግኸው ታገኘዋለህ፤ ከተውከው ግን እርሱም ለዘላለም ይተውሃል።

10. ለመቅደስ የሚሆን ቤት እንድትሠራ እግዚአብሔር የመረጠህ መሆኑን አሁንም ዐስብ፤ በርትተህም ሥራ።

11. ከዚያም ዳዊት የቤተ መቅደሱን መመላለሻ፣ የሕንጻውን፣ የዕቃ ቤቶቹን፣ የፎቁንና የውስጥ ክፍሎቹን እንዲሁም የማስተስረያውን ቦታ ንድፍ ለልጁ ለሰሎሞን ሰጠው።

12. ደግሞም መንፈስ ቅዱስ በልቡ ያሳደረውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አደባባይ፣ በዙሪያው ያሉትን ክፍሎች ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃ ቤቶችና የንዋየ ቅድሳቱን ግምጃ ቤቶች ንድፍ ሁሉ ሰጠው፤

13. እንዲሁም የካህናቱንና የሌዋውያኑን አመዳደብ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎት ሥራና ለአገልግሎቱ ስለሚጠቀምባቸው ዕቃዎች ሁሉ መመሪያ ሰጠው።

14. ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉትን የወርቅ ዕቃዎች ሁሉ መጠን፣ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉትን የብር ዕቃዎች ሁሉ መጠን አሳወቀው፤

15. እንደየመቅረዙ አገልግሎት ዐይነት ለወርቁ መቅረዞችና ለቀንዲሎቻቸው የሚሆነውን የእያንዳንዳቸውን የወርቅ መጠን፣ ለብሩ መቅረዞችና ለቀንዲሎቻቸው የሚያስፈልገውን የእያንዳንዳቸውን የብር መጠን፣

16. ለያንዳንዱ፣ ኅብስተ ገጽ ጠረጴዛ የሚያስፈልገውን የወርቅ መጠን፣ ለእያንዳንዱም የብር ጠረጴዛ የሚያስፈልገውን የብር መጠን፣

17. ለሹካዎቹ፣ ለጐድጓዳ ሳሕኖቹ፣ ለማንቆርቆሪያዎቹ የሚያስፈልገውን ንጹሕ የወርቅ መጠን፣ ለእያንዳንዱ የብር ሳሕን የሚያስፈልገውን የብር መጠን፣

18. ለዕጣኑ መሠዊያ የሚሆነውን የጠራ ወርቅ መጠን እንዲሁም ክንፎቻቸውን ዘርግተው የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸፍኑትን ከወርቅ የተሠሩትን የኪሩቤል ሠረገሎች ንድፍ ሰጠው።

19. ዳዊትም፣ “ይህ ሁሉ፣ በእኔ ላይ ባለው በእግዚአብሔር እጅ በጽሑፍ ተገለጠልኝ፤ የንድፉንም ዝርዝር እንድረዳ ማስተዋልን ሰጠኝ” አለ።

20. ደግሞም ዳዊት ልጁን ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ በል በርታ፤ ጠንክር፤ ሥራውንም ጀምር። አትፍራ፤ ተስፋም አትቊረጥ፤ እግዚአብሔር አምላኬ ከአንተ ጋር ነውና፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎት ሥራ እስኪፈጸም ድረስ አይተውህም፤ አይጥልህም።

21. ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ ሁሉ የሚያስፈልጉት ካህናትና ሌዋውያን ምድብም ዝግጁ ነው። በሁሉም የእጅ ሙያ የሠለጠኑ ፈቃደኛ ሰዎች በሥራው ሁሉ ይረዱሃል። ሹማምቱና ሕዝቡ ሁሉ ትእዛዝህን ይፈጽማሉ።”