ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 26:17-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. በአንዱ ዘብ ጥበቃ ትይዩ ሌላ ዘብ ጥበቃ ነበረ፤ በየቀኑም በምሥራቅ በኩል ስድስት፣ በሰሜን በኩል አራት፣ በደቡብ በኩል አራት፣ በዕቃ ቤቱ በኩል በአንድ ጊዜ ሁለት ሌዋውያን ይጠብቁ ነበር።

18. በምዕራቡ በኩል የሚገኘውን አደባባይ ደግሞ በመንገዱ ላይ አራት፣ በአደባባዩ ላይ ደግሞ ሁለት ሆነው ይጠብቁ ነበር።

19. እንግዲህ የቆሬና የሜራሪ ዘሮች የሆኑት በር ጠባቂዎች ድልድል ይህ ነበር።

20. ከሌዋውያን መካከል አኪያ የእግዚአብሔር ቤት ግምጃ ቤትና የተቀደሱት ዕቃዎች የሚቀመጡበት ግምጃ ቤት ኀላፊ ነበረ።

21. የለአዳን ዘሮች፣ በለኣዳን በኩል ጌድሶናውያን የሆኑትና ለጌድሶናዊው ለለአዳን ቤተ ሰቦች አለቆች የሆኑት የለአዳን ዘሮች እነዚህ ነበሩ፤ ይሒኤሊ፣

22. የይሒኤሊ ወንዶች ልጆች፣ ዜቶምና ወንድሙ ኢዩኤል። እነዚህም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት ኀላፊዎች ነበሩ።

23. ከእንበረማውያን፣ ከይስዓራውያን፣ ከኬብሮናውያን፣ ከዑዝኤላውያን፤

24. የሙሴ ልጅ የጌርሳም ዘር የሆነው ሱባኤል የግምጃ ቤቱ የበላይ ኀላፊ ነበረ።

25. በአልዓዛር በኩል የሚዛመዱት፤ ልጁ ረዓብያ፣ ልጁ የሻያ፣ ልጁ ኢዮራም፣ ልጁ ዝክሪ፣ ልጁ ሰሎሚት።

26. ሰሎሚትና የሥጋ ዘመዶቹ ንጉሥ ዳዊት፣ የቤተ ሰቡ ኀላፊዎች፣ የሻለቆችና የመቶ አለቆች እንዲሁም ሌሎች የሰራዊቱ አዛዦች ቀድሰው ላቀረቧቸው ንዋያተ ቅድሳት ኀላፊዎች ነበሩ።

27. በጦርነት ከተገኘውም ምርኮ ከፊሉን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ማደሻ እንዲሆን ቀደሱት።

28. ባለ ራእዩ ሳሙኤል፣ የቂስ ልጅ ሳኦል፣ የኔር ልጅ አበኔር፣ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የቀደሱትን ሁሉና እንዲሁም ሌሎቹን ንዋያተ ቅድሳት ሰሎሚናትና ቤተ ዘመዶቹ ይጠብቁ ነበር።

29. ከይስዓራውያን፤ ከናንያና ወንዶች ልጆቹ ከቤተ መቅደሱ ውጭ ባለው ሥራ በእስራኤል ላይ ሹማምትና ዳኞች ሆነው ተመደቡ።

30. ከኬብሮናውያን፤ ሐሽብያ፣ ጠንካራና ጐበዝ የሆኑ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ በሚገኘው የእስራኤል ምድር ላለው የእግዚአብሔር ሥራና ለንጉሡም አገልግሎት ኀላፊዎች ሆነው ተመደቡ።

31. በኬብሮናውያን በኩል በቤተ ሰቦቻቸው የትውልድ መዝገብ መሠረት ይሪያ አለቃቸው ነበረ። በዳዊት ዘመነ መንግሥት በአርባኛው ዓመት መዛግብቱ ተመርምረው ስለ ነበር፣ በገለዓድ ውስጥ ኢያዜር በተባለ ቦታ ከኬብሮናውያን መካከል ጠንካራ ሰዎች ሊገኙ ችለዋል።

32. ይሪያም ጠንካሮችና የቤተ ሰባቸው አለቆች የሆኑ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ሥጋ ዘመዶች ነበሩት። ንጉሥ ዳዊትም እነዚህን የእግዚአብሔር ለሆነውና የንጉሡም በሆነው ጒዳይ ላይ ሮቤልን፣ ጋድንና የምናሴን ነገድ እኵሌታ ኀላፊ አድርጎ ሾማቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዜና መዋዕል 26