ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የቤተ መቅደሱ በር ጠባቂዎች

1. የቤተ መቅደሱ በር ጠባቂዎች አመዳደብ፤ከቆሬያውያን ወገን፤ ከአሳፍ ወንዶች ልጆች አንዱ የሆነው የቆሬ ወንድ ልጅ ሜሱላም።

2. ሜሱላም ወንዶች ልጆች ነበሩት፤የመጀመሪያው ዘካሪያስ፣ሁለተኛው ይዲኤል፣ሦስተኛው ዮዛባት፣አራተኛው የትኒኤል፣

3. አምስተኛው ኤላም፣ስድስተኛው ይሆሐናን፣ሰባተኛው ኤሊሆዔናይ።

4. ዖቤድኤዶምም እንደዚሁ ወንዶችልጆች ነበሩት፤የመጀመሪያው ሸማያ፣ሁለተኛው ዮዛባት፣ሦስተኛው ኢዮአስ፣አራተኛው ሣካር፣አምስተኛው ናትናኤል፣

5. ስድስተኛው ዓሚኤል፣ሰባተኛው ይሳኮር፣ስምንተኛው ፒላቲ፤እግዚአብሔር ዖቤድኤዶምን ባርኮታልና።

6. እንዲሁም ልጁ ሸማያ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም በቂ ችሎታ ስለ ነበራቸው የአባታቸው ቤት መሪዎች ሆነው ነበር።

7. የሽማያ ወንዶች ልጆች፤ ዖትኒ፣ ራፋኤል፣ ዖቤድ፣ ኤልዛባድ፤ ዘመዶቹ ኤሊሁና ሰማክያም እንደዚሁ በቂ ችሎታ ነበራቸው።

8. እነዚህ ሁሉ የዖቤድኤዶም ዘሮች ሲሆኑ፣ እነርሱም ሆኑ ወንዶች ልጆቻቸውና ቤተ ዘመዶቻቸው ሥራውን ለመሥራት በቂ ችሎታ ነበራቸው። የዖቤድኤዶም ዘሮች ባጠቃላይ ሥልሳ ሁለት ነበሩ።

9. ሜሱላም በቂ ችሎታ ያላቸው ወንዶች ልጆችና ቤተ ዘመዶች ነበሩት፤ ቊጥራቸውም ባጠቃላይ ዐሥራ ስምንት ነበረ።

10. ከሜራሪ ወገን የሆነው ሖሳ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ የመጀመሪያው ሽምሪ ነበረ፤ የበኵር ልጅ ባይሆንም እንኳ፣ አባቱ ቀዳሚ አድርጎት ነበር።

11. ሁለተኛው ኬልቅያስ፣ ሦስተኛው ጥበልያ፣ አራተኛው ዘካርያስ፤ የሖሳ ወንዶች ልጆችና ቤተ ዘመዶቹ ባጠቃላይ ዐሥራ ሦስት ነበሩ።

12. የቤተ መቅደሱም ጠባቂዎች በአለቆቻቸው ሥር ተመድበው ልክ እንደ ቤተ ዘመዶቻቸው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ ለማከናወን ምድብ ተራ ነበራቸው።

13. ለእያንዳንዱም በር ወጣት ሽማግሌ ሳይባል ለሁሉም እኩል ዕጣ ተጣለ።

14. የምሥራቁ በር ዕጣ ለሴሌምያ ወጣ። ከዚያም ምክር ዐዋቂ ለሆነው ለልጁ ለዘካርያስ ዕጣ ጣሉ፤ እርሱም የሰሜኑ በር ደረሰው።

15. የደቡቡ በር ዕጣ ለዖቤድኤዶም ሲወጣ፣ የግምጃ ቤቱ ዕጣ ደግሞ ለልጆቹ ወጣ።

16. የምዕራቡ በርና በላይኛው መንገድ ላይ የሚገኘው የሸሌኬት በር ዕጣዎች ለሰፊንና ለሖሳ ወጣ።

17. በአንዱ ዘብ ጥበቃ ትይዩ ሌላ ዘብ ጥበቃ ነበረ፤ በየቀኑም በምሥራቅ በኩል ስድስት፣ በሰሜን በኩል አራት፣ በደቡብ በኩል አራት፣ በዕቃ ቤቱ በኩል በአንድ ጊዜ ሁለት ሌዋውያን ይጠብቁ ነበር።

18. በምዕራቡ በኩል የሚገኘውን አደባባይ ደግሞ በመንገዱ ላይ አራት፣ በአደባባዩ ላይ ደግሞ ሁለት ሆነው ይጠብቁ ነበር።

19. እንግዲህ የቆሬና የሜራሪ ዘሮች የሆኑት በር ጠባቂዎች ድልድል ይህ ነበር።

የግምጃ ቤት ኀላፊዎችና ሌሎች ሹማምት

20. ከሌዋውያን መካከል አኪያ የእግዚአብሔር ቤት ግምጃ ቤትና የተቀደሱት ዕቃዎች የሚቀመጡበት ግምጃ ቤት ኀላፊ ነበረ።

21. የለአዳን ዘሮች፣ በለኣዳን በኩል ጌድሶናውያን የሆኑትና ለጌድሶናዊው ለለአዳን ቤተ ሰቦች አለቆች የሆኑት የለአዳን ዘሮች እነዚህ ነበሩ፤ ይሒኤሊ፣

22. የይሒኤሊ ወንዶች ልጆች፣ ዜቶምና ወንድሙ ኢዩኤል። እነዚህም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት ኀላፊዎች ነበሩ።

23. ከእንበረማውያን፣ ከይስዓራውያን፣ ከኬብሮናውያን፣ ከዑዝኤላውያን፤

24. የሙሴ ልጅ የጌርሳም ዘር የሆነው ሱባኤል የግምጃ ቤቱ የበላይ ኀላፊ ነበረ።

25. በአልዓዛር በኩል የሚዛመዱት፤ ልጁ ረዓብያ፣ ልጁ የሻያ፣ ልጁ ኢዮራም፣ ልጁ ዝክሪ፣ ልጁ ሰሎሚት።

26. ሰሎሚትና የሥጋ ዘመዶቹ ንጉሥ ዳዊት፣ የቤተ ሰቡ ኀላፊዎች፣ የሻለቆችና የመቶ አለቆች እንዲሁም ሌሎች የሰራዊቱ አዛዦች ቀድሰው ላቀረቧቸው ንዋያተ ቅድሳት ኀላፊዎች ነበሩ።

27. በጦርነት ከተገኘውም ምርኮ ከፊሉን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ማደሻ እንዲሆን ቀደሱት።

28. ባለ ራእዩ ሳሙኤል፣ የቂስ ልጅ ሳኦል፣ የኔር ልጅ አበኔር፣ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የቀደሱትን ሁሉና እንዲሁም ሌሎቹን ንዋያተ ቅድሳት ሰሎሚናትና ቤተ ዘመዶቹ ይጠብቁ ነበር።

29. ከይስዓራውያን፤ ከናንያና ወንዶች ልጆቹ ከቤተ መቅደሱ ውጭ ባለው ሥራ በእስራኤል ላይ ሹማምትና ዳኞች ሆነው ተመደቡ።

30. ከኬብሮናውያን፤ ሐሽብያ፣ ጠንካራና ጐበዝ የሆኑ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ በሚገኘው የእስራኤል ምድር ላለው የእግዚአብሔር ሥራና ለንጉሡም አገልግሎት ኀላፊዎች ሆነው ተመደቡ።

31. በኬብሮናውያን በኩል በቤተ ሰቦቻቸው የትውልድ መዝገብ መሠረት ይሪያ አለቃቸው ነበረ። በዳዊት ዘመነ መንግሥት በአርባኛው ዓመት መዛግብቱ ተመርምረው ስለ ነበር፣ በገለዓድ ውስጥ ኢያዜር በተባለ ቦታ ከኬብሮናውያን መካከል ጠንካራ ሰዎች ሊገኙ ችለዋል።

32. ይሪያም ጠንካሮችና የቤተ ሰባቸው አለቆች የሆኑ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ሥጋ ዘመዶች ነበሩት። ንጉሥ ዳዊትም እነዚህን የእግዚአብሔር ለሆነውና የንጉሡም በሆነው ጒዳይ ላይ ሮቤልን፣ ጋድንና የምናሴን ነገድ እኵሌታ ኀላፊ አድርጎ ሾማቸው።